የትንሣኤ በዓል በሰላም መከበሩን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

31

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን የትንሣኤ በዓል በሰላም እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርቧል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኅብረተሰቡን ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ ተቋማዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ሁለንተናዊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ከዋዜማው ጀምሮ ልዩ ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸው የትንሣኤ በዓልን ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ለማክበር ከክልል እስከ ቀበሌ ልዩ ስምሪት በመስጠት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጥምረት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

የኅብረተሰቡን ሰላም የሚያውኩ ችግሮች እንዳይከሰቱ በገቢያ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች አካባቢዎች ልዩ ጥበቃ መደረጉን ገልጸዋል።

ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የትንሣኤ በዓል በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች ከዋዜማው እስከ በዓሉ ዕለት ያለ ምንም ችግር በሰላም መከበሩንም አንስተዋል።

ለበዓሉ ሰላማዊነት በየደረጃው ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ተወጥቷል ያሉት ኀላፊው የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጥምረት በዓሉ በሰላም እንዲውል ለነበራቸው ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” የኢትዮጵያ ትንሣኤ ቅርብ ነው፣ እኛም እናያለን፣ ልጆቻችንም ይወርሳሉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ አረፉ።