
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) 80 የንብ ቀሰም ዕፅዋት እና ለማር ምርት ዕድገት የሚረዱ ምርምሮችን ማቅረቡን የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ማርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል የንብ ተመራማሪና እንስሳት ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አያሌው ግርማይ የማዕከሉ የንብ ምርመር ከ10 ዓመታት በፊት የማር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተቋቋመ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ በምርምሩ 35 ዓይነት የንብ ዝርያዎችንና 80 የሚደርሱ የንብ ቀሰም ዕፅዋትን ማግኘት መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ የንብ በሽታና መፍትሔዎችን፣ የዋግ የንብ ዝርያዎች ባሕሪያትንና የማር ዓይነትን መለየትም ተችሏል፡፡ ሽግግርና ዘመናዊ ቀፎችን መሥራት፣ ንብን በማባዛት የአርሶ አደሮችን የማነብ ሥራ በተግባር እንዲቀየር ማድረግም ባለፉት ዓመታት ተከናውነዋል፡፡ በየዓመቱ ለአናቢዎች ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሦስት አካባቢዎች የንብ ምርምር ማዕካላት ያሉት ሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል አንድን እናት ንብ በመክፈል እስከ አምስት ኅብረ ንብ የማባዛት ልምድን ለአናባቢዎች በማሸጋገር የንብና የማር ምርት ዕድገት እንዲኖረው ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም ለ100 አናቢዎች የንብ ዕፅዋት አቅርቦትና የማባዛት ቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ መቻሉንም አቶ አያሌው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ከምርምሩ ትምህርት ከወሰዱ አርሶ አደሮች መካከል የሰቆጣ ወረዳ ጃንቅቫ ቀበሌ ነዋሪው አቶ እማኙ አያሌው አንዱ ናቸው፡፡ ‘‘ከ1997 ዓ.ም በፊት ንብ ማነብ ሥራ አልጀመርኩም ነበር፤ ዘመናዊ ቀፎ ከተጀመረ በኋላ በምርምሩ በተሰጠኝ ትምህርት ከሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች ጎን ለጎን ንብ በማነብ ላይ ነኝ’’ ብለዋል፡፡ አቶ እማኙ አምስት ኅብረ ንቦችን በዘመናዊ ቀፎ አድርገው የቀሰም ዕፅዋት በተከሉበት ጓሯቸው ውስጥ እየተንከባከቡ ነው፡፡ ባለፈው ጥር 2012 ዓ.ም ብቻ ከአንድ ቀፎ ንብ በአንድ ጊዜ የምርት ዘመን እስከ አምስት ሺህ ብር ከማር ሽያጭ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡ አቶ እማኙ በባህላዊ ቀፎ አንድ መቶ የንብ መንጋ ከመያዝ ይልቅ አምስት በዘመናዊ የንብ ቀፎ መያዝ ይበልጣል ብለው ያምናሉ፡፡ የምርምር ማዕከሉ የሚሰጣቸውን ስልጠና አድንቀው፤ ዋግ ካላት የንብ ሀብት አንጻር ስልጠናው ለሁሉም መሰጠት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ጥጉየ በአስተዳደሩ 66 ሺህ 627 ኅብረ ንብ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከሉ በድርቅ መስፋፋት ምክንያት በንብ ሀብቱ ላይ የሚፈጠረውን የሀብት ማሽቆልቆል ለመግታታ እየሠራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ንቦችን ማባዛት እና በቂ የምግብና ውኃ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ እየሠራን ነው’’ ያሉት ኃላፊው በተለይ በተፋሰስ ልማቶች ዙሪያ በንብ ማነብ ለተሠማሩ ወጣቶች የንብ ማባዛት ልምድን በማካፋሉ ለሕይወታቸው ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ እየረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2011/2012 የማር ምርት ዘመን 994 ቶን ለማምረት ታቅዶ እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ 922 ቶን የማር ምርት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ‘‘ጥራቱን የጠበቀ አንድ የዋግ ነጭ ማር አንድ ኪሎ እስከ 300 ብር ሲሸጥ ነበር’’ ያት አቶ ታደሰ የተገኘውን የማር ምርት በአማካይ ዋጋ 200 ብር ቢሰላ እንኳ 18 ሚሊዮን 440 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ነው ያመላከቱት፡፡
ምንም እንኳ የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርመሩም ሆነ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ከዘርፉ ተስፋ እንዳለ ቢገልጹም ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ከንብ ሀብቱ ገሚሱን እንኳ መጠቀም እንዳልተቻለ ያመላክታል፡፡
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በጥቅሉ ካለው 66 ሺህ 627 ኅብረ ንብ 5 ሺህ 743 በዘመናዊ ቀፎ፣ 991 በሽግግር ቀፎ ሲገኝ 90 በመቶ የሚሆነው 59 ሺሕ 893 ደግሞ በባህላዊ ቀፎ የሚገኝ ነው፡፡ ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ በአማካይ 29 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት ይቻላል፤ ከአንድ ባህላዊ ቀፎ ደግሞ በአማካይ 9 ኪሎ ግራም ማር ይገኛል፡፡ ይህም የ20 ኪሎ ግራም የማር ልዩነት እንዳለ ያሳያል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት እንኳ ሁሉንም ወደዘመናዊ ቀፎ መቀየር ቢቻል ኖሮ 19 ሚሊዮን 321 ሺህ 83 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ይህም አሁን ባለው አማካኝ የገበያ ዋጋ በ200 ብር ቢሰላ 386 ሚሊዮን 436 ሺሕ 600 ብር ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር ማለት ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የንብ ሀብቱ ባለማዘመኑ በየዓመቱ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚያገኘው ገቢ 22 እጥፍ ያጣል ማለት ነው፡፡ ታዲያ በንብ ማነብ ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን ተችሏል ማለት እንዴት ይቻላል? የንብ ሀብቱ እያለ ወደዘመናዊ ቀፎ የመቀየር አቅም እና ተነሳሽነትስ እንዴት ታጣ? ቀጣይ ትኩረትና መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ናቸው?
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡