ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

58

ባሕር ዳር: ሚያዚያ: 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የርእሰ መሥተዳድሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልእክት፦

ትንሳኤ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ መቃብርን አጥፍቶ የተነሳበት በዓል ነው። ጠላት ተደምስሶ የሰው ልጆች ሁሉ ድል የታወጀበት፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከጉስቁልና ወደ አዲስ ሕይወትና ተስፋ እንዲሁም ወደ ፍጹም ደስታና ሰላም የተሸጋገርንበት ዕለትም ነው።

ከትንሳኤው ፈተናን በጽናት መሻገር፣ ጨለማን ወደ ብርሃን መቀየር እንደሚቻል እንረዳለን። በትግስትና በትሕትና ማለፍን እንማራለን። ዛሬ ያጋጠሙን ችግሮችም ለትውልድ የማይሻገሩ፣ የሚታለፉና የሚፈቱ ናቸው። ፈተናዎችን ወደ እድል ለመቀየር የሕዝባችንን ሰላም ማጽናትና ልማታችን ማፋጠን አለብን።

ከግጭት ያተረፉ፣ ከጥፋት የበለጸገ ሀገር ሆነ ሕዝብ የለም። እንደ ሕዝብ በህብርና በትብብር እንደ ሀገር በአንድነት መቆም ያስፈልጋል። ዛሬ በእርስ በርስ ግጭት የምናባክነው ጊዜ በትውልድ ቅብብሎሽ ሒደት ውስጥ ከወርቅና ከአልማዝ በላይ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው ጠንቅቆ መረዳት ይገባል።

ሰላምና ልማት የሁለንተናዊ ብልጽግናችን መዳረሻዎች ናቸው። የሕዝባችን መሠረታዊ ፍላጎትም የሚረጋገጠው በልማት ነው። ልማት ደግሞ የሰላም ውጤት ነው። የሁሉም ስኬቶቻችን መሰረት የሆነውን ሰላማችን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም፤ በቅንጅትና በትብብር መስራት ይኖርብናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የካበተ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የመተባበር ባሕልና እሴት ባለቤቶች ነን። ለተቸገሩ ማካፈል፤ ጧሪ ለሌላቸው መረዳትና ማዕድ ማጋራት ትናንትም ሆነ ዛሬ ሁነኛ የአብሮነታችን መገለጫ ነው።

ስለሆነም በዓሉን ስናከበር ባሕላችን እና ኃይማኖታዊ እሴታችን በሚፈቅደው መሠረት የተቸገሩ ወገኖቻችን በማሰብ በአብሮነት እና በመተባበር እንድናሳልፍ፤ በዓሉም የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆንልን እመኛለሁ።

መልካም በዓል!

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበበዓል ጊዜ በጋራ በማሳለፍ የኢትዮጵያን እሴት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ።