አክፍሎት ምንድን ነው?

57

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሙነ ሕመማት የጭንቅ እና የፍዳ ሳምንት ናት። ይች ሳምንት የ5 ሺህ 500 የብሉይ ዘመን ሥርዓት የሚታሰብባትም ናት።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዓመተ ፍዳ ወይንም ከዓመተ ኩነኔ ወደ ዓመተ ምህረት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጣ ስለ ሰው ልጅ የተቀበላቸውን ሕማማት የሚታሰብበት ሳምንት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ፈለገ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም አገልጋይ እና የቅኔ እና ቅዳሴ መምህር ሄኖክ አሸናፊ ሰሙነ ሕማማት ከሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ኢየሱስ ክርስቶስን ለመያዝ አይሁድ የመከሩበት እና ምክራቸውን ያጸኑበት ነው ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይዙ እህል ላለመቅመስ ክፉ መሐላ የተማማሉበት፤ ኢየሱስ ክርስቶስን የያዙበት፣ የገረፉበት እና በዕለተ አርብ በቀራንዮ የሰቀሉበት ሳምንትም ነው ይላሉ መምህሩ።

በዚህ ሳምንት በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ የተለያዩ ሥርዓቶች የሚከናወኑ ሲኾን ከዚህ ውስጥ ደግሞ አክፍሎት አንዱ እንደኾነ ተናግረዋል።

አክፍሎት ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሱበትን ስቃዮች አስመልክቶ በጾም መቆየት መኾኑን ነው የገለጹት።

የበረቱ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ከተያዘባት ሰዓት ጀምሮ እስከ ትንሳኤው ድረስ ያሉትን ሦስት ማዕልት እና ሦስት ሌሊት ያከፍላሉ ብለዋል። ካልኾ ደግሞ በዕለተ አርብ ከስግደት በኋላ ምዕመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ብቻ በመቅመስ እስከ እሁድ ወይንም ትንሳኤ ድረስ ይፆማሉ ነው ያሉት።

ከሰባት ዓመት በላይ የኾነ የቻለ የሃይማኖቱ ተከታይ ሁሉ መፆም እንደሚችልም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቅዳሜ ስዑር አማኞች ለምን ቄጤማ ያስራሉ?
Next article“እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)