
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቅዳሜ ስዑር በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዕለት ነው ይላሉ የአራቱ ጉባኤ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም ገብረ ኪዳን።
እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ያረፈባት የመጀመሪያዋ ቅዳሜ “ሰንበት ዐባይ” በመባል ትታወቃለች ብለዋል።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የፍጥረቱ ራስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሲል ሕመም እና ሞትን የተቀበለው ክርስቶስ በመቃብር ያረፈው በዚህ ዕለት ነው ብለዋል።
በተለይም ይህች ዕለት “ሥዑር” የተባለችው አማኞች በዓመት አንድ ቀን ሙሉ ስለሚፆሙ እንደኾነም ገልጸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ሐዋርያቱ እህል እና ውኃ በአፋቸው እንዳላዞሩ አመሳጥረው ይናገራሉ።
በመኾኑም አማኞች የዚህን ዕለት በሐዘን እና ትንሣኤን በመናፈቅ በመፆም እና በጸሎት ያሳልፋሉ ብለዋል።
እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት አማኞች ከአርብ ጀምሮ በመጾም እህል እና ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ ነው ያሉት። ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም ያልቻሉ ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን እንደሚጾሙ አስረድተዋል።
ከሆሣዕና ማግሥት ጀምሮ እስከ ስቅለተ አርብ ድረስ በጾም እና በስግደት ያሳለፉ አማኞች ቅዳሜ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ይሠበሠባሉ ብለዋል።
የጠዋቱ ጸሎት ሲጠናቀቅም ካህናቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ” እያሉ የምሥራች ምልክት የኾነውን ቄጤማ ለተሰበሰቡት አማኞች እንደሚያድሉም አብራርተዋል።
ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም ይህ ቄጤማ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ከምድር ላይ መድረቁን ያበሰረችው ርግብ ይዛው ከመጣችው ቄጤማ ጋር የተያያዘ ምሳሌነት አለው ብለዋል።
ልክ በዚያን ጊዜ ቄጤማ የደስታ ምልክት እንደነበረው ሁሉ፣ ዛሬም በክርስቶስ ሞት የኃጢዓት ሞት ከሰው ልጆች እንደተወገደች ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ የምሥራች ታስተላልፋለች ነው ያሉት።
አማኞችም ይህንን የምሥራች በመቀበል ቄጤማውን በግንባራቸው ያስራሉ ብለዋል።
በዚህም መንገድ የክርስቶስ ተከታዮች ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ ገነት መመለሳቸውን በመግለጽ የትንሣኤን በዓል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ያከብራሉ።
ይህ የቅዳሜ ስዑር ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕምነት እና ትውፊት አካል እንደኾነም አብራርተዋል።
አማኞች የኢየሱስን ሕመም እና ሞት በማስታወስ ለትንሣኤው በናፍቆት እንዲዘጋጁ የሚያደርግ መንፈሳዊ ዝግጅት ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!