“ገዳዩን መሳሪያ አስቀምጡና በሃይማኖት፣ በአንድነት፣ በስምምነት ሰላምን አምጡ፣ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጥሪ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

28

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለትንሳኤ በዓል ቃለ በረከት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ሕይዎት በዓለመ ፍጡራን ውስጥ ከሚገኘው ነገር ሁሉ ተወዳዳሪ የሌላት ድንቅ ነገር ናት፤ ሕይዎት ኣካልን የማንቀሳቀስ፣ የማመዛዘን፣ የመወሰን እና የመሥራት ሃብተ ጸጋ ያላት ልዩ ናት ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ሕይዎት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ወይም የሚመስል ጠባይ አላት፤ ሕይዎት ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የተጣበቀ ወይም የተሳሰረ ግንኙነት አላት ነው ያሉት።

ሕይዎት ፈጣሪን እና የፈጣሪ ርዳታን ስትሻ የመኖርዋ ምስጢርም ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝ ጸጋ ስላላት ነው ብለዋል። ሕይዎት መልካም ስትሠራ ደስተኛ፣ ክፉ ስትሠራ ደግሞ ስቅቅተኛ የምትኾንበት ምክንያትም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛት ጸጋ ስለሚነግራት ነው፣ መልካምን መውደድ፣ ክፉን መጥላት የእግዚአብሔር የማይለወጥ ጠባይ ስለኾነ ነው ያሉት። ክፉን ሠርታ ከእርሱ ጋር በደስታ እና በነጻነት መኖር በፍጹም አትችልምና ብለዋል።

ሕይዎት የማትጠፋ ብትኾንም የመሞት ስጋት ያልተለያት ፍጡር ናት፤ በተለይም እግዚአብሔርን የበደለች ዕለት ከባድ የሞት አደጋ ያጋጥማታል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ሞት የሥጋ ሳይኾን ከእግዚአብሔር እና የእግዚአብሔር ከኾነው ሁሉ መለየት ነው፤ የሕይዎት ከባዱ ሞትም ይኽ ነው ብለዋል።

የጥንቱ ሐጥያት ሳይበቃን በየሰዓቱ በምንፈጽመው ክፉ ተግባር በበደል ላይ በደል እየጨመርን በመቀጠላችን በጨለማ ላይ ተጨማሪ የጨለማ ጥላ አክለንበታል ነው ያሉት። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሞታችን ወይም ከእግዚአብሔር መለየታችን የሰፋ እና የከፋ እንዲኾን አድርጎታል ብለዋል ቅዱስነታቸው።

ጌታችን የትንሣኤ በኵር ኾኖ ተነሥቷል፤ ከትንሣኤውም በኋላ ለዘላለም በሕይዎት ይኖራል። በቀጣይም ጊዜው ሲደርስ እኛ ተከታዮቹ የእርሱን ዓይነት ትንሣኤ ተነሥተን በማያልቅ ኃይለ ሕይዎት ከሱ ጋር ለዘላለም በሕይዎት እንኖራለን፤ ጌታችን ያሳየን የሕይዎት መንገድ ይኸው ነው ብለዋል።

ይህ ሕይዎት ከሁሉም ሕላዌ ሕይዎት የላቀ እና የበለጠ ጣዕም ያለው ዘላለማዊ እና ድንቅ ሕይዎት ነው፤ ይህ ሕይዎት ከስጋት፣ ከስሕተት፣ ከቅጣት እና ከሞት ፍርሐት ነጻ የኾነ፣ በፍጹም ነጻነት እና ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም የሚያኖር ሕይዎት ስለኾነ ሁላችንም ወደዚህ ሕይዎት ለመድረስ በእምነት እንተጋለን ነው ያሉት።

ዘር ሳይኖር ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ ሕይዎታዊ ትንሣኤም ያለ ሃይማኖት እና ሥነ ምግባር ሊገኝ እንደማይችልም ገልጸዋል። “መልካም ያደረጉ ለሕይዎት ትንሣኤ ይነሣሉ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ” እንዳለ ጌታችን የሕይዎትን ትንሣኤ የሚያገኝ ያመነ፣ የተጠመቀ እና መልካም ሥራን የሠራ እንጂ የተነሣው ሁሉ አለመኾኑ ግልጽ ነው ብለዋል።

የመጨረሻው ዕድል የተንጠለጠለው እምነትን ተከትለን በምንሠራው ሥራ ላይ ነው፣ ዛሬ ከሰው አእምሮ በእጅጉ እየራቀ የሚገኘው ይኽው እምነት እና ሥነ ምግባር ነው፤ ሰዎች ከእምነት እና መልካም ሥነ ምግባር በራቁ ቁጥር ሕይዎት መራራ እንድትኾን ትገደዳለች ነው ያሉት።

እኛ ኢትዮጵውያን ከጥንት ጀምሮ በእምነት እና ሥነ ምግባር እየተመራን፣ በደልን በይቅርታ እየዘጋን፣ እስከ ጋብቻ በሚዘልቅ ባሕለ ዕርቅ ደምን እያደረቅን፣ በወንድማማችነት ፍቅር ተስማምተን በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት እንዳልኖርን፣ እነሆ ዛሬ ለታላቅነታችን በማይመጥን ሁኔታ መለያየት፣ መጣላት እና እርስ በርስ መገዳደል ዕለታዊ ተግባራችን አድርገን እንገኛለን ነው ያሉት።

ይህ በጣም አሳዛኝ ክሥተት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው
ይህንን ሳናስተካክል የምናከብረው በዓለ ትንሣኤም እዚህ ግባ የሚባል ደስታ ሊያስገኝልን እንደማይችል የታወቀ ነው ብለዋል።

እየኾነ ያለው ሁሉ ማንንም አይጠቅምም፤ በዕርቅ፣ በይቅርታ እና በውይይት የማይፈታ ችግር ያለ ይመስል ይህን ያህል መጨካከን እንዴት እንደ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል? አሁንም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የምንማጸነው? እባካችሁ እኛው ራሳችን ሸምጋይ እና ተሸምጋይ ኾነን ችግሮቻችንን ለመፍታት በብርቱ እንሥራ መፍትሔም እናምጣ ብለዋል በመልዕክታቸው።

መሳሪያ አንሥታችሁ እርስ በርስ በመገዳደል የምትገኙ ወገኖቻችን እባካችሁ ቆም ብላችሁ አስቡና ሰላም እና ዳቦ አጥቶ ለተቸገረው ሕዝባችሁ ስትሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል ስጡ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኾኗን በትክክል የሚያረጋግጥ ሰላማዊ መፍትሔ በማስቀመጥ ለአንድነትዋ እና ለዕድገትዋ አጥብቃችሁ ጣሩ፤ ግጭት እና መለያየት ከሚያጠፋን በቀር ምንም ዓይነት ጥቅም ሊሰጠን እንደማይችል ብዙ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም ነው ያሉት።

“ገዳዩን መሳሪያ አስቀምጡና በሃይማኖት፣ በአንድነት፣ በስምምነት እና በጭንቅላት ኃይል ሰላምን አምጡ፤ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጥሪ ነው” ብለዋል።

በልዩ ልዩ ምክንያት ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በየአካባቢው የሚገኙ ወገኖቻችን በትንሣኤው በዓል ተጽናንተውና እፎይ ብለው በደስታ እንዲያሳልፉ ካለን ከፍለን በመመገብ እና በማልበስ እንድንደርስላቸው አባታዊ መልዕክት እናስተላልፋለን ነው ያሉት።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጉብኝቱ ኢትዮጵያ አስፈላጊ ሀገር መኾኗን ያረጋገጠ ነበር” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)
Next articleበቅዳሜ ስዑር አማኞች ለምን ቄጤማ ያስራሉ?