የስቅለት በዓል የበደልናቸውን ብቻ ሳይኾን የበደሉንን ጭምር ይቅር የማለት ምሳሌ መኾኑን መጋቢ ሐዲስ መምህር አሸተ ዜናዊ ተናገሩ።

18

ሁመራ: ሚያዚያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስቅለት በዓል የበደልናቸውን ብቻ ሳይኾን የበደሉንንም ይቅር ማለትን የምንማርበት ታላቅ በዓል መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ሐዲስ መምህር አሸተ ዜናዊ ተናግረዋል።

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ቦታ ካላቸው አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንደኛው ነው። ይህ ጾም ክርስቶስ ተወልዶ በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ለሰው ልጅ ዋጋ የከፈለበት በመኾኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ የአምላኩን ምግባራት እና ሕማማት እያሰበ ወቅቱን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና በምጽዋት ያሳልፈዋል ብለዋል መጋቢ ሐዲስ መምህር አሸተ ዜናዊ።

ይህ የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምነት እንደኾነም ተናግረዋል። ይህ ሳምንት ካለፉት የጾሙ ሳምንታት በተለየ ሁኔታ ሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ጾም፣ በስግደት እና ጸሎት የሚበረታበት መኾኑን መጋቢ ሐዲስ መምህር አሸተ ገልጸዋል። በተለይ ዕለተ አርብ አምላክ ጻድቅ ኾኖ እያለ እንደ በደለኛ የተንገላታበት፣ የተገፋበት፣ የተተፋበት፣ በደረቅ መሬት ላይ ተጎትቶ፣ መራራ ሀሞት ተግቶ፣ እጆቹን በችንካር እና ጎኑንም በጦር ተወግቶ በመስቀል ላይ የሞተበት ዕለት መኾኑን አስረድተዋል።

“ሕዝበ ክርስቲያኑ ከክርስቶስ ፍቅርን፣ ትህትናን እና ለሌሎች ዋጋ መክፈልን እና ለባለ እንጀራ እስከ ሞት ድረስ መታመንን ገንዘቡ ሊያደርግ እንደሚገባ” አሳስበዋል። አምላክ ከዙፋኑ የወረደው ምድር እና ሰማይን፣ ሰው እና መልዓክትን ለማስማማት እና የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ባርነት ነጻ ለማውጣት መኾኑን በመረዳት ሁሌም ቢኾን አንዳችን ለአንዳችን መኖር አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያዊነት ነባር ባሕል በሰላም መኖር ነበር ያሉት መጋቢ ሐዲስ ጥል እና መለያየትን ትተን በአብሮነት ለመኖር ክርስቶስ የከፈለንን ዋጋ ማስታወስ ይኖርብናል ብለዋል። የፆሙን ወራት በፆም እና በጸሎት እንዳሳለፉት የነገሩን ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው የሁመራ ከተማ የእምነቱ ተከታዮች ናቸው።
ክርስቶስ በዛሬው ዕለት የሞተው ዘር፣ ሃይማኖት እና ብሔር ሳይለይ የሰውን ልጅ ሁሉ ለማዳን ነው ብለዋል።

እኛ ሁላችንም ሰላምን እና ፍቅርን ገንዘብ በማድረግ በአንድነት መኖርን ከክርስቶስ መማር አለብን ነው ያሉት። አሚኮ በሁመራ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅድስት ድንግል ማርያም አብያተ ክርስቲያናት የተገኘ ሲኾን ምዕመናን በጸሎት እና በስግደት ቀኑን አስበውት እየዋሉ እንደኾነ ተመልክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዕለተ አርብ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ፍቅሩን የገለጸበት ዕለት ነው።
Next articleመዕመኑ ልቦናውን ለፍቅር እና ለይቅርታ ክፍት ማድረግ እንዳለበት መምህረ መምህራን የንታ በጽሐ ዓለሙ ተናገሩ።