
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያና ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡
በሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተወከለው የኢትዮጵያ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ-ኮሚቴ ስብሰባ ከግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ሲመክር ሰንብቷል፡፡ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሱዳን የልዑካን ቡድን ደግሞ በሱዳን ሪፐብሊክ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ ነው የተመራው፡፡ ኮሚቴው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው፣ በድንበር ጉዳዮች እና አዋሳኝ አካባቢዎች የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ነው ሲመክር የነበረው፡፡
የፖለቲካ ምክክሩ በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ግንኙነትን፣ ሰላምን፣ አብሮ መኖርን እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የረጅም ጊዜ ግንኙነቶችን በሚያጠናክር መንፈስ መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በውይይቱ በተለይ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የፀጥታና የደኅንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተም የሕዝቦችን አብሮነትና የግንኙነቱን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት እንደተካሄደ ነው የተገለጸው፡፡
በአገራቱ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አቅጣጫ እንደተቀመጠም ተገልጧል፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተረጋግተው ያለምንም መስተጓጎል የእርሻ ሥራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባም በምክክሩ ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣ የደኅንነት ስጋት እና የነዋሪዎችን የተረጋጋ ሕይወት የሚያውኩ አዳዲስ የፀጥታ ኃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ መስተካከል እንዳለባቸውም አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡ የሁለቱ አገራት አጎራባች የአስተዳደር አካላትም በየጊዜው እየተገናኙ ልዩነቶችን በማጥበብ በጋራ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከር እንዳለባቸውም መግባባት ላይ እንደተደረሰ ነው የተገለጸው፡፡
ሁለቱ ወገኖች ቀጣዩን የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በመጪው ሰኔ 2012 ዓ.ም አጋማሽ በካርቱም ለማድረግ መስማማታቸውም ታውቋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡