
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አዳም ሕግ በመተላለፉ ምክንያት የመጣበትን ሞት ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፤ ከልጅ ልጁ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እና በሦስተኛው ቀን ተነስቶ እንዳዳነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች።
የስቅለት በዓል ታሪክ እና አከባበር አንደምታ ምን እንደኾነ በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር ቃለ ጽድቅ አየነው አብራርተውልናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱም ቀዳሚው አዳም የወደቀው በእንጨት (በዕጽ) በመኾኑ በእንጨት ለመመለስ ነው ብለዋል። ዕጸ በለስ የገደለችውን ዕጸ መስቀል አዳነው ማለት እንደኾነም ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቦታ ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጪ የኾነበት ምክንያት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ከቁጥር 33 ጀምሮ እንደተገለጸው የወይን አትክልት ባለቤት ወደ አትክልት ሠራተኞቹ እረኞችን ሲልክ ጥሪውን አክብረው ከመምጣት ይልቅ መልዕክተኞችን ይደበድቡ ነበር ብለዋል።
የሰው ደም አትክልት እንደሚያደርቅ ስላሰቡ ከአትክልቱ ቦታ አውጥተው መግደላቸውን የጠቀሱት ቃለ ጽድቅ ምስጢሩ ግን በጥላቻ ምክንያት ክርስቶስን ከልቦናቸው አውጥተው እንደሚገድሉት ለማመላከት ነው ብለዋል። በዚያ ዘመን መስዋዕት ሲሰው ከከተማ አውጥተው ነበርና ክርስቶስም ለበጎቹ ምትክ ኾኖ ስለመጣ ነው የአዳም የራስ ቅል ባለበት የተሰቀለው ብለዋል።
በቅንዋተ መስቀል ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅ እና እግሮቹ የተቸነከሩባቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሔዋን እጁን በእጇ ቆርጣ ስለነበረ እና በእግሯ ወደ በለሱ በመሄዷ እጅ እና እግሩን በመቸንከር ካሣ መክፈሉንም ገልጸዋል።
የሦስት፣ የስድስት እና የዘጠኝ ሰዓታት ስግደትስ ትርጓሜው ምንድን ነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ደግሞ የስቅለት ዕለት በሦስት፣ በስድስት እና በዘጠኝ ሰዓት እንደሚሰገድ ገልጸዋል መምህር ቃለ ጽድቅ። ይህም በቤተክርስቲያን ከሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ውስጥም እነዚህ ጊዜያት መኖራቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ሰዓታት ጎልተው የተመረጡበት የተለያዩ አንደምታዎች ቢኖሩም ክርስቶስ ሊሰቀል ቁርጥ ውሳኔ የተላለፈበት ጊዜ ሦስት ሰዓት፣ አዳም በለስ በልቶ ከገነት የወጣባት እና ኢየሱስ ክርስቶስም የተሰቀለው በስድሥት ሰዓት እንዲሁም ቅዱስ ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በገዛ ፈቃዱ የለየው በዘጠኝ ሰዓት በመኾኑ ነው ብለዋል። የሰው ልጅ በጸሎቱ ያንን እያሰበ ለመጸለይም ይሰገዳል ብለዋል።
ለምን የማይሞተው ሞተ ይባላል? ለሚለው ጥያቄ መምህሩ ሲመልሱ የማይሞተው ሞተ የሚባለው ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ ክርስቶስን ሲገንዙት ዝም ብለው እንደ ሩቅ ብዕሲ (ሰው) ሲገንዙት ነበር ነው ያሉት። ክርስቶስም ዐይኖቹን ገልጦ ለምን ዝም ብላችሁ እንደ ሩቅ ብዕሲ ትገንዙኛላችሁ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው፣ ዘኢይመውት እያላችሁ ገንዙኝ ብሎ በፈቃዱ ማሸለቡን ጠቅሰዋል። ይህም ሕያው ነው ማለት ነው ብለዋል።
ክርስቶስ ሞት የማይገባው እንደኾነ እና ሞት ለመለኮት ባሕርይውም አይስማማውም፤ መለኮት በስጋ ተሰቀለ፣ ተገረፈ ነው የሚባለው ነው ያሉት። በስቅለቱ ከጎኑ ስለፈሰሰው ደም እና ውኃ ሲናገሩም አንድ ዐይና የነበረ ለንጊኖስ የተባለ ሰው በክርስቶስ ላይ ሲመከርበት ከምክሩ ባለመግባት ተለይቶ ጫካ ውሏል ብለዋል። መያዙን ሲያውቅ ግን መሰቀሉ የማይቀር ከኾነ ከሰው ላለመለየት ሲሮጥ ሂዶ ኢየሱስ ክርስቶስን በጦር ወጋው ይላሉ። ከተወጋው የክርስቶስ ጎን የተፈናጠረው ትኩስ ደም እና ትኩስ ውኃም የለንጊኖስን ዐይን ፈወሰው ብለዋል።
እግዚአብሔር ውለታ ስለማይረሳ ከሱ መከራ አልውልም ብሎ ጫካ የዋለውን ሰው በኋላ ላይ በጦር ቢወጋውም በደም እና ውኃው ዐይኑን ብርሃን እንዳደረገለት ገልጸዋል።
ዛሬ ላይ በቤተ ክርስቲያን ደመ ገቦ እና ማየ ገቦ የሚባለው በዚያ ጊዜ የፈሰሰውን ትኩስ ደም እና ውኃ ነው ብለዋል። በቁርባን ጊዜ ከቅዱስ ሥጋው ጋር የምንቀበለው እና የምንጠመቅበት ክቡር ደሙ የምንለው የያኔው ደም እና ውኃ ነው ብለዋል።
በዕለተ ዓርብ በስቅለቱ የተሠራው በርካታ ሥራ እና ተዓምር የዛሬ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን