
ሰቆጣ: ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ቀን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ በደብረ ገነት መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በፆም፣ በጸሎት እና በስግደት እየታሰበ ነው።
የአዳም ልጆች 5 ሺህ 500 ዘመን ተፈርዶባቸው የነበረውን የሞት ፍርድ በሕይዎት ለመተካት ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ የሰው ልጅ ፍቅር ስቦት ስለ ዓለም አንድነት እና ስለ ሰላም ሲል የተሰቀለበት ዕለት መኾኑን የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ ተናግረዋል።
“የክርስቶስን ሕማማተ መስቀል የሚያስብ ሁሉ እርስ በርሱ ሊዋደድ ይገባል” ሲሉ የገለጹት ደግሞ የደብረ ገነት መድኃኒዓለም ደብር ዋና አሥተዳዳሪ እና የድጓ መምህሩ መልአከ ገነት ጸጋ ዘአብ ታደሰ ናቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የተጣሉትን አስታርቋል፤ ያሉት የድጓ መምህሩ ይህንን የስቅለቱን ዕለትም የመስቀሉን በረከት ለማግኘት በፍጹም አንድነት እና በመተሳሰብ ሕመሙን እና ሞቱን ማሰብ ማክበር ይገባል ነው ያሉት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ዕለትም በደብረ ገነት መድኃኒዓለም ደብር በፆም፣ በጸሎት እና በስግደት እየታሰበ ነው።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን