በባሕር ዳር ከተማ 461ለሚኾኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ።

13

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ እንዳሉት ለትንሳኤ በዓል ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ ሃብት በማሰባሰብ ከ500 በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደርጓል።

ከዚህ ውስጥ ለ461 የኅብረተሰብ ክፍሎች 25 ኪሎ ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይት እና ዶሮ ድጋፍ የተደረገ ሲኾን ለ100 ሰዎች ደግሞ የገንዘብ ስጦታ ተበርክቷል።

በሃብት ማሰባሰቡ ማኅበረሰቡ ያሳየው ተሳትፎ የቆየውን የመተጋገዝ እና የመደጋገፍ እሴት ያሳየ መኾኑን መምሪያ ኀላፊዋ ገልጸዋል። በቀጣይም ተጋላጭ ሴቶች፣ ሕጻናት እና አረጋውያን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ይህንን መልካም እሴት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

አጠቃላይ የትንሳኤ በዓልን መሠረት በማድረግ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ 18 ሚሊዮን 387 ሺህ 613 ብር ተሰብስቧል። በዚህ ሃብትም ለ46 ሺህ 636 የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ በበዓላት ወቅት የሚደረገው የመተጋገዝ እና የመረዳዳት ባሕል የቀደመውን እሴት እንዲጠናከር አድርጓል።

አሁን ላይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትንሳኤ በዓልን በሰላም እንዲውሉ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ሃብት በማሰባሰብ የማስተላለፍ ሥራ ተሠርቷል። አሁንም እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመወጣት ይበልጥ መተጋገዝ እና መተዛዘን የሚጠይቅበት ጊዜ በመኾኑ ከበዓላት ውጭ ጭምር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ለሰላም እንዲቆምም ጠይቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ የኔማር አላምረው አንዷ ሲኾኑ የተደረገው ድጋፍ በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲውሉ አድርጓል። ሌላኛው ድጋፍ የተደረገላቸው ታሪክ ገረመው ድጋፉ በዓሉን እንደማንኛው ሰው እንዲውሉ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። የመረዳዳት ዕሴት የኢትዮጵያውያን መልካም መገለጫ በመኾኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቃል በተግባር የተፈጸመባት አርብ!
Next articleየክርስቶስን ሕማማተ መስቀል የሚያስብ ሁሉ እርስ በርሱ ሊዋደድ ይገባል።