ቃል በተግባር የተፈጸመባት አርብ!

54

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዕለተ አርብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ቀን ነው። የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት ድንቅ ዕለት ናት ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለ ማርያም አሳይ።

ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነጻ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የኾነበት የደስታ ቀን ስለመኾኑም ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለ ማርያም ያስረዳሉ። ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ስለመኾኑም ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለማርያም ነግረውናል።

የስቅለት አርብም ይሏታል ሊቃውንቱ ዕለተ አርብን። ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለ ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ኾኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለባት ዕለት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

ይህች ዕለትም መልካሟ አርብም ትባላለች። ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምኅረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል ነው ያሉት።

የስቅለት አርብም እንደምትባል የተናገሩት ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለ ማርያም የዓለም ሁሉ መድኃኒት የኾነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም እና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ኾኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት ኾኖ የዋለባት ዕለት በመኾኗ የስቅለት ዓርብ ተብላለች ብለዋል።

ከክርስቶስ ስቅለት በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፤ በተለይ በሮማውያን እና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረና ይላሉ።

በዚች ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር፣ ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምኅረት ምልክት፣ የሕይወት አርዓያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ፣ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ ስላደረገውና በዕለተ አርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሟ ዓርብ እንደተባለችም አብራርተዋል፡፡

በዚህ ዕለትም ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለጽ ተአምራት ስለማሳየቱም ሊቀ አዕላፍ አባ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል።

ከተአምራቱም መካከል ፀሐይ ጨልማለች፣ ከዋክብት ረግፈዋል፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዷል፣ ምድር ተናውጣለች፣ መቃብሮች ተከፍተዋል፣ ሙታን ተነስተዋል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየትንሳኤ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ 461ለሚኾኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ።