በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን መያዙን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

21

ጎንደር: ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን መያዙን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታውቋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም የእገታ ወንጀልን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በተቀናጀ የጸጥታ አካላት እየተወሰደ ባለው የእገታ ወንጀልን የመከላከል ተግባር በእገታ ወንጀል የተጠረጠረው ቀናው ክንዴ የተባለ ግለሰብ ከሦስት ግብረ አበሮቹ ጋር መያዙንም አስታውቀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከጎንደር ከተማ ማኅበረሰብ ጋር የጸጥታ ኀይሉ በሠራው ሥራ ሰባት አጋቾችን ለሕግ ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል። ከእነዚህም መካከል ሦሥቱ ወንጀለኞች መኾናቸው ተረጋግጦ ማረሚያ ቤት መግባታቸውን ተናግረዋል። ቀሪዎቹ በሕግ ክትትል ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የጸጥታ አካሉ ባደረገው ክትትል ሰባት የእገታ ወንጀሎችን ማስቀረት መቻሉን የተናገሩት ኀላፊው ሦሥት የታገቱ ሕፃናት ያለ ምንም ክፍያ ወደ ወላጆቻቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አስታውቀዋል። በእገታ ወንጀል የሚሳተፉ ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ተመሳስለው የሚኖሩ መኾናቸውም ተገልጿል።

የእገታ ወንጀልን ለመከላከል ማኅበረሰቡ የብሎክ አደረጃጀት ጥበቃን በማጠናከር ለሰላሙ በባለቤትነት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከተማ አሥተዳደሩ የእገታ ወንጀልን ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የኾነው ቀናው ክንዴ ከዚህ ቀደም በሦሥት የእገታ ወንጀሎች መሳተፉን ገልጿል። ሌላኛው ተጠርጣሪ ዓለም አስማረ ደግሞ በእገታ ወንጀል ከተሳተፉ ግለሰቦች ጋር መተባበሩን ተናግሯል።

ተጠርጣሪዎቹ በፈጸሙት ድርጊት መጸጸታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በመስቀል ተሰቀለ?
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወልድያ ዲስትሪክት ለአቅመ ደካማ ወገኖች ለበዓል ድጋፍ አደረገ።