
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መስቀል ከአዲስ ኪዳን በፊት የወንጀለኛ መቅጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው ደግሞ በፋርስ ወይንም በአኹኗ ኢራን ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ፈለገ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም አገልጋይ፣ የቅኔ እና የቅዳሴ መምህር ሄኖክ አሸናፊ እንዳሉት የፋርስ ሰዎች “ኦርሙዝድ” የተባለ የመሬት አምላክ ያመልኩ ነበር።
ፋርሶች አንድን ወንጀለኛ ሲቀጡ የሚፈሰው ደም መሬት ላይ ካረፈ “አምላካችን ይረክሳል” ብለው ስለሚያምኑ በሀገሪቱ ያልተፈቀደ ወይንም የማይገባ ሥራ የሠራን ወንጀለኛ ሁሉ ከመሬት ከፍ አድርገው በመስቀል ቅርጽ በተሠራ እንጨት ላይ ይቀጡ ነበር።
ቅጣቱ ቀስ በቀስ ወደ ሮማ ግዛት ጭምር ተስፋፍቶም ነበር። በኦሪቱ ሥርዓት ቅጣታቸውን በመስቀል ላይ የሚቀበሉ ሰዎችም ርጉማን እና ውጉዛን ተደርገው ይታዩ ነበር።
ይህንንም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሙሴ “ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፣ እንዲሞትም ቢፈረድበት፣ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር” ሲል ነግሮታል።
እዚህ ላይ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚሞት የተረገመ ከኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ? የሚል ጥያቄ ይነሳል።
ኢየሱስ ክርስቶስ “እንደ ወጡ ሳይመለሱ፣ እንደወደቁ ሳይነሱ ይቅሩ” ሳይል የሰውን ልጅ ለመፈለግ ከሰማይ ሰማያት ወርዶ በመንፈስ ቅዱስ ግብር በማኅፀነ ድንግል ማርያም ተፀነሰ።
ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። ሠላሳ ዓመት እንደሞላው በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ ሄዶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ።
አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት፣ ሰባ ሁለቱን አርድዕት እና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት መረጠ።
አዲስ ሕግ ወንጌልንም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር አስተማረ። በመጨረሻም ለሰው ልጅ ኃጢአት ተላልፎ በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ።
በዚህም ዕለት ፅንስ ኾኖ በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ጀምሮት የነበረውን የማዳን ሥራ በመስቀል ላይ ፈጸመው።
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተው ስለ ሰው ልጅ እርግማን ተላልፎ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ኃጢአት በመስቀል ላይ በመሸከሙ የሰውን ልጅ ከመርገመ ሥጋ፣ ከመርገመ ነፍስ ነጻ እንዲኾን አድርጓል።
በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ምን ተገኘ?
➽. ሕይወት ተገኝቶበታል።
በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሰው ልጅ ሞት ነግሶበት ነበር። ከክርስቶስ በኋላ ግን በቤዛነቱ ሞት ስለተሻረ የሰው ልጅ አጥቶት የነበረውን ሕይወት አግኝቶታል።
➽. የሕይወት ምግብ ተገኝቶበታል።
ኃጢአት ወደ ዓለም ገብቶ ሞትን ያመጣው በመብል ምክንያት ስለኾነ የሕይወት ምግብ ተገኝቶበታል።
➽.ሰላም ተገኝቶበታል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” ብሎ እንደተናገረው ፍጹም የኾነውን ሰላም በመስቀል ላይ ሰጥቷል።
➽. አዲስ ሰውነት ተገኝቶበታል። በመርገመ ሥጋ፣ በመርገመ ነፍስ አርጅቶ የነበረው የሰው ልጅ ሰውነት አዲስ የኾነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው።
➽. የሰው ልጅ ታርቆበታል። በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ይኖር የነበረው የሰው ልጅ እርሱ ክሶ በቤዛነቱ መልሶ ታርቋል።
➽. መስቀል ኃይል ነው። የኢየሱስ ክርስትስ ኃይሉ ተገልጦ የማዳን ሥራውን የፈጸመው በመስቀል ተሰቅሎ ነው። በመኾኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው የተፈተተበት እና ክቡር ደሙም የፈሰሰበት መስቀል ስለ ክርስቶስ የከበረ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን