ላጋጠመው ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ምላሽ መፈለግ እንደሚገባ በሕገ መንግሥቱ ማርቀቅ ሂደት የተሳፉት ተናገሩ፡፡

205

በሕገ መንግሥቱ ትርጉም ጥያቄ ላይ በማርቀቅ ሂደት የተሳተፉ ሰዎች ሙያዊ አስተያዬት አቅርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ የባለሙያዎች አስተያዬት ለማሰባሰብ በቀረበ ጥሪ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጽሑፍ የሙያ አስተያዬት ያቀረቡ ግለሰቦችና ተቋማት ይፋ ሆነዋል፡፡

በተደረገው ጥሪ መሠረት በጽሑፍ አስተያዬታቸውን ያቀረቡ ተቋማትና ባለሙያዎችን የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ልዩ ረዳት አቶ ከበበ ታደሰ አቅርበዋል፡፡

ዛሬ በተደረገው ውይይት ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው የተባሉ ግለሰቦችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ የሐሳብ አስተዋፅኦ የነበራቸው ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ጸሐፊ የነበሩት አምባሳደር ተስፋየ አቢሶ፣ የኮሚሽኑ አባል የነበሩት አባሳደር ታየ አጽቀሥላሴና አባሳደር አብዱላዚዝ አህመድ በሕገ መንግሥቱ የመጽደቅ ሂደትና አጠቃላይ እሳቤዎቹ ዙሪያ የነበሩ ውይይቶችን በማስታወስ አብራርተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ራስ ገዝነትንና የተገደበ የመንግሥት ስልጣትን የማክበርና የሕዝብን ሉዓላዊነት መሠረት አድርጎ የቀረበ እንደነበር ማብራሪ ሰጥተዋል፡፡

‘‘በረቂቁ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የምርጫ ሂደት እንዲሁም መሰል ጉዳዮች እየተነሱ ጥልቅ ውይይት ይደረግባቸው ነበር’’ ያሉት ደግሞ በሳዑዲ ዐረቢየኢትዮጵያ አባሳደር አብድላዚዝ አህመድ ናቸው፡፡ እንደተናገሩት ከሆነ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም ባይታወጅም ምርጫ በመርሀ ግብሩ መሠረት መካሄድ እንዳለበት ለውይይት ቀርቧል፡፡ እንዲህ የሕዝብን ጤንነት አደጋ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ በከፊልም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከለክል ስለሚችል ምርጫ ሊካሄድ አይገባም የሚል ሐሳብ በአንድ አባል በውይይቱ ወቅት ተስቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሐሳቦቹ ላይ ግን በቂ ውይይት ተደርጓል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት የሥልጣን ክፍተት እንዳኖር ራሱን የቻለ ውይይት ባይኖርም የምርጫ ዘመናቸው ያበቃ የምክር ቤቶችና አስፈፃሚ አባላት በሕዝብ የተመረጡ በመሆናቸው ሁኔታው እስኪቀየር የሚቆዩ ይሆናል በሚል የተቀመጠ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ አስገዳጅ ናቸው ተብለው ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ጉዳዮች በአብዛኛው በወቅቱ ልኬታ የታዩ እንደሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ኅያው ሰነድ በመሆኑ ሊወለድ፣ ሊያድግና ሊሻሻል የሚችል መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርና የፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን የተለያዩ የተደረጉት እንዲህ ዓይነት እርግጠኛ ያልተሆነባቸው ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን በማመላከተም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous articleበኩር ግንቦት 10/2012
Next articleየነዋሪዎችን የተረጋጋ ሕይወት የሚያውኩ የፀጥታ ኃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ መስተካከል እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡