
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ” … ሚሻ ሚሾ! ሚሻ ሚሾ!
እሜቴ ስለ ስቅለቱ ፣
ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ…፤
ሆ ሚሻ ሚሾ! ሚሻ ሚሾ!…
አንድ አውራ ዶሮ፣
እግሩን ተሰብሮ፣
እዘኑለት፣
ስላውዳመት፣
እሜቴ ይነሱ ፣
ይወሳወሱ፣
ካደረው ዱቄት ትንሽ ይፈሱ” ከሚሻ ሚሾ ግጥም የወሰድነው ነው።
ታዳጊዎች ሲቀጥሉም፦
ጨው ጨው_ ማጣፈጫው፣
ዘይት ዘይት- መሰልቀጫው። በማለት በርበሬ እና ዘይት ይቀበላሉ።
“ታዳጊዎች ከዓመት ዓመት ያድርስልን” በማለት አመስግነው በተመሳሳይ ክዋኔ እና ጭፈራ ወደ ቀጣዩ ቤት ይሄዳሉ።
የሃይማኖቱ ሊቃውንት ኢየሱስ ክርስቶስ “ውሾ ውሾ” እየተባለ የደረሰበትን መሰደብ፣ መገረፍ እና መንገላታት በማሰብ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ዕለቱን ‟ሚሻ ሚሾ” በማለት ያስታውሱታል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ታዳጊ ቢኾነኝ ዳኙ (በወላጅ እናቱ ይሁንታ ቃለ ምልልስ ማድረጋችን ልብ ይሏል) ከጓደኞቹ ጋር በመኾን ሚሻ ሚሾ ማለቱን ይናገራል።
ሚሻ ሚሾ ሲሉ እናቶች ዱቄት፣ ዘይት፣ በርበሬ እና ጨው እንደሰጧቸው ነግሮናል፡፡ ዱቄቱን በአዋቂዎች አስቦክተው እና ዳቦ አስጋግረው በጋራ እንደተመገቡት አጫውቶናል፡፡
ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሕፃን ሃብተማርያም ሙሉቀን ”ለምን ሚሻ ሚሾ እንደምል ባላውቀውም ባለፉት ዓመታት ብያለሁ” ነው ያለው።
ዘንድሮም በወላጅ አባቱ በትር አዘጋጅቶ ሚሻ ሚሾ ከጓደኞቹ ጋር ማለቱን ሕፃን ሃብተማርያም ተናግሯል።
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጂያ ኀላፊ መጋቢ ምስጢረ ሙሉቀን ቁምላቸው እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት አገዛዝ ወጥተው ወደ ርስታቸው በሚጓዙበት ወቅት ለምግብነት ዱቄት፣ ቂጣ እና ውኃ ይዘው እንደነበረ በስቅለት ዕለት በሚባለው “ሚሻ ሚሾ ” ይታወሳል ነው ያሉት፡፡
ሚሻ ሚሾ አይሁድ የተደበደበበት ምሳሌ ነው ። ለዚህም ነው ሕጻናት እና ታዳጊዎች የቤቱን የበር መቃ በመደብደብ የአይሁድን መደብደብ የሚዘክሩት ይላሉ፡፡
የሚሻ ሚሾ በሕፃናት እና ታዳጊዎች ለመከናዎኑ ምክንያቱ አዋቂዎች ጦመኛ መኾናቸው እንደኾነ መጋቢ ምስጢረ ነግረውናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተቀበለው መከራ፣ የተሰደበው ስድብ፣ የተገረፈው ግርፋት ለሃይማኖቱ ተከታዮች ሙሉ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ ስለተፈለገም ነው “ውሾ ውሾ” የሚለውን “ሚሻ ሚሾ” ወደሚለው ስያሜ በማምጣት ታዳጊዎች የተዥጎረጎረ በትር ይዘው ዱቄት መለመናቸው በማለት መጋቢ ምስጢር ያስረዱት፡፡
አሚኮ የ“ሚሻ ሚሾ” ጨዋታ በዚህ ዘመን ለምን ተቀዛቀዘ የሚል ጥያቄ ለመጋቢ ምስጢረ አቅርቧል። እሳቸውም “ትውፊቱን በውል አለማወቅ ነው” ካሉ በኋላ ወላጆች እና የዘርፉ ምሁራን የየዘመናቸውን ትውልድ በማስተማር ባሕሉ እንዲቀጥል ሊያደርጉ እንደሚገባ መጋቢ ምስጢረ አሳስበዋል፡፡
ሕጻናት ሥርዓቱን ከፈጸሙ በኋላ ተሠባሥበው በመብላት በመጫዎትም አንድነታቸውን ያጠናክራሉም ነው ያሉት። ሚሻ ሚሾ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ሰላምን የሚያሰፍን፣ አንድነትን የሚያጠናክር፣ መረዳዳትን እና አብሮ መብላትን የሚያመጣ ነው ብለዋል።
እያጣነው ያለውን ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር የመመለሻው ቁልፉም ይኽው ነው ሲሉ መጋቢ ምስጢር ይመክራሉ ።
ታዳጊዎች እና ሕጻናት ሲሠበሠቡ እነርሱ እና ወላጆቻቸውም አንድነት እና ፍቅር ይኖራቸዋል። ወዲህ ደግሞ አብሮ መሥራትን፣ መተሳሰብን ያደረጃልና ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በመኾኑም ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የጨዋታ ሥርዓቱን እና ትውፊቱ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል መጋቢ ምስጢር፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን