
ጎንደር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን አስመልክቶ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም የክልሉ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አስቻለ አላምሬ ክልሉ ከገባበት የሰላም እጦት እንዲወጣ የክልሉ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት
ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየሠራ መኾኑን አመልክተዋል።
የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበርም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ኀላፊው የተናገሩት። ኀብረተሰቡም አካባቢውን በመጠበቅ ለሰላም ዘብ በመኾን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። በዓሉ በሰላም እንዲከበር የኅብረተሰቡ ድርሻ የጎላ ነው ያሉት ኀላፊው ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ አካላት ማሳወቅ ይኖርበታል ብለዋል።
የሚሊሻ ኀይሉ ከሌሎች የጸጥታ ዘርፎች ጋር በመቀናጀት በሠራው ሰላምን የማስከበር ተግባር ለውጦች እየመጡ እንደኾነ አብራርተዋል። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል ያሉት ኀላፊው ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች እና ለጸጥታ መዋቅሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን