
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት በተለምዶው 22 በተባለ አካባቢ የተገነባው ባለአራት ወለል የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዓለምፀሐይ ሽፈራው አስታውቀዋል።
ሕንጻው በገቢዎች ሚኒስቴር፣ በጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሁም በከተማ አሥተዳደሩ ውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን ትብብር የተገነባ መኾኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። በዛሬው ዕለትም 117 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው 65 የመኖሪያ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ እና በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች መተላለፋቸውን ነው ያነሱት።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸው ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ችግራቸውን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዕለቱ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በችግር ውስጥ ለነበሩ እና ለልማት ተነሽዎች 446 ቤቶችን ማስተላለፍ መቻሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በከተማ አሥተዳደሩ 39 ሺህ ቤቶችን ማስተላለፍ መቻሉንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል። ለቤት ግንባታው ድጋፍ ላደረጉ ባለሃብቶች እና ተቋማትም ከንቲባዋ አመሥግነዋል። የተላለፉት የመኖሪያ ቤቶችም ሳሎን፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ እንዲሁም የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች ናቸው ተብሏል።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር ዓይናለም ንጉሤ በከተማ አሥተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች የዜጎችን ሕይዎት በዘላቂነት የሚቀይር እና የከተማዋን ገጽታ የሚያጎሉ ናቸው ብለዋል።
የመኖሪያ ቤቶችን ከማስረከብ ባሻገር የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለእነዚህ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍም ተደርጓል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!