
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ድጋፉ በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የተደረገ ሲኾን ለአንድ ሰው 25 ኪሎ ግራም የምግብ ዱቄት እና 5 ሊትር ዘይት ነው። ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ የሺወርቅ መሰሉ እና ወይዘሮ ስለእናት መለሰ በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ የሺወርቅ ”ከሰው ጋር መኖሬን አወቅሁ” ብለዋል። ሀገራችን ሰላም ኾኖ እንዲህ ተዛዝነን ለመኖር ያብቃን ብለዋል። ኮርፖሬሽኑም እኛን ፈልጎ በዓል ስላዋለን እናመሰግናለን ብለዋል። ወይዘሮ ስለእናትም የኑሮ ውድነቱ አስጨንቋቸው በነበረ ጊዜ ለበዓል መዋያ ድጋፍ ስለተደረገላቸው አመስግነዋል።
ሌላኛው የድጋፉ ተጠቃሚ አቶ ማርዬ ምትኩ በበኩላቸው በመንገድ ላይ ቁጭ ብለው የሰውን ክብደት በሚዛን በመመዘን እንደሚተዳደሩ ገልጸው ልጆቻቸውን በዓል የሚያውሉበት ስለሌላቸው ጨንቋቸው እንደነበር ተናግረዋል። ድጋፉን በማግኘታቸውም ጭንቀታቸው መቅለሉን ጠቅሰው ድጋፉን ላደረጉላቸው አመስግነዋል።
ችግረኛ በሁሉም ቦታ አለ፤ እናም ሁሉም በያለበት ቢረዳዳ መልካም ነውም ብለዋል። የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ ኮርፖሬሽኑ ለትርፍ ከመሥራት በተጨማሪ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በሕንጻ ግንባታ ሥራው ማኅበረሰቡን ከመጥቀም በተጨማሪ በግንባታ እና ችግረኞችን በመርዳት ሕዝብን መደገፉን ጠቅሰዋል።
ለችግረኛ ወገኖች በዓል መዋያ ድጋፍ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኀላፊዎች ወስነው የምግብ ዱቄት እና ዘይት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። ድርጅታችን ስኬታማ የሚኾነው ከሕዝብ መሃል ኾነን እና ሕዝብን እየደገፍን ጭምር ስንሠራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽኑ በሚሠራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረግን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!