በደብረ ብርሀን ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።

20

ደብረ ብርሃን: ሚያዚያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በደብረ ብርሀን ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግምቱ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ ነክ እና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

በከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሥተባባሪነት ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመኾን ለ1 ሺህ 340 የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው ድጋፉ የተደረገው።

ድጋፍ ከተደረገላቸዉ መካከል አስር አለቃ እሸቴ መላኩና ኪያ ተክሉ ድጋፉ የትንሳኤ ለማክበር የሚያግዝ በመኾኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትም ለወገን ደራሽ መኾናቸዉን ያስመሰከሩበት በመኾኑ ምስጋናችን ይድረሳቸዉ ብለዋል።

የሆፕ ፎር ጠባሴ የእርዳታ ማኅበር መስራችና አሥተባባሪ መለሰ አባተ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸዉንና አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ የማኅበሩ አባላት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ማኅበሩ በተለያየ ምክንያት ችግር ላጋጠማቸዉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ ነዉ ብለዋል።

ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በጋራ በመኾን የተደረገው ድጋፍ የትንሳኤ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ የተደረገ መኾኑን ያነሱት የአማኑኤል የልማት ድርጅት የፕሮጀክት አሥተባባሪ ሰለሞን ታደሰ እነዚህ ወገኖች የራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸዉ ለማስቻል ሥልጠና እየተሰጥ መኾኑን ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡና ረጅ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጥናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ ግምቱ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፊኖ ዱቄት፣ የዘይት፣ የጥራጥሬና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዚያትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰል ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆንኑ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ስንታየሁ ሀይሉ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጎንደር ከተማ ውስጥ ለሚገኙ አቅም የሌላቸው ወገኖች ድጋፍ ተደረገ።
Next articleዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ለአቅመ ደካማ ወገኖች የትንሣኤ በዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል።