
ጎንደር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለትንሳኤ በዓል ከ800 ሺህ ብር በላይ ወጭ ያደረጉበትን የምግብ ቁሳቁስ በከተማዋ ለሚኖሩ የተቸገሩ ነዋሪዎች ድጋፍ አድርገዋል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ 300 ለሚኾኑ በጎንደር ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ነዋሪዎች ነው ድጋፉን ያደረጉት።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይነህ ይደግ ለጋሽ ድርጅቶቹ ለትንሳኤ በዓል መዋያ የዘይት፣ የፊኖ ዱቄት እና የዶሮ መግዣ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
ኀላፊው ለዚህ ድጋፍ ከ800 ሺህ ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ገልጸዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ለከተማዋ ነዋሪዎች በበዓላት ወቅት ከአሁን በፊትም ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ኀላፊው አስታውሰዋል።
በዓሉን በመተጋገዝ እና በመደጋገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ የገለጹት አቶ በላይነህ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ኀይሉ የሁልጊዜ ተግባሩን እየከወነ ይገኛል ብለዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገንዘብ መምሪያ የፕሮጀክት ክትትል እና በይነ መንግሥታት አስተባባሪ አበበ ካሤ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ 27 የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመደበኛነት ማኅበረሰቡን እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በበዓል ወቅትም ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ከድርጅቶቹ 800ሺህ ብር የሚገመት ወጭ መደረጉን የገለጹት አቶ አበበ ይህንን ተግባራቸውን ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወይዘሮ ፍርኑስ ቢሰጥ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በዓላትን ለማክበር ይቸገሩ ነበር። አሁን ግን ከነበረባቸው ችግር እንዲወጡ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመሥግነዋል።
ሌላዋ ድጋፍ የተደረገላቸው ወይዘሮ አስረበብ ተስፋ የተደረገላቸው ድጋፍ በዓልን በቤታቸው እንዲያከብሩ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:-ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን