
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሰሞነ ሕማማት በመባል የሚታወቀው ይህ ሳምንት የመከራ፣ የሕማም እና የጨለማ ሳምንት እንደኾነ ይታሰባል ይላሉ የትርጓሜ መጻሕፍት መምህሩ ዘላለም በላይ። ከእነዚህ ቀናት መካከል ጸሎተ ሐሙስ እየተባለች የምትጠራው የዛሬዋ ቀን አንዷናት ብለዋል መምህር ዘላለም።
ሐሙስ ቀን የሚታሰበው ጸሎተ ሐሙስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን የተፈጸሙበት ነው የሚሉት መምህሩ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ቁርባን የሠራበት ቀን በመኾኑ ከሌሎቹ ቀናት በተለየ ኹኔታ ቅዳሴ ይከናወናል ብለዋል። አማኞች ቅዳሴውን አስቀድሰው እና ሥርዓቱን ከፈጸሙ በኋላ ሲመለሱ ጉልባን የሚባል ከተቀላቀለ እህል የተዘጋጀ ንፍሮ ይመገባሉ ነው ያሉት።
መምህር ዘላለም የዚህ ዝግጅት ትውፊት የመጣው ከእስራኤል ባሕል ነው ባይ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ክርስቶስ ሳይወለድ ኦሪት በመባል የሚታወቀውን የእስራኤላውያንን ሕግ ተቀብለው በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን ያመልኩ ስለነበር ብዙ የእስራኤል ባሕል እና ትውፊቶች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይንጸባረቃሉም ይላሉ።
ከእነዚህ ትውፊቶች አንዱ ጉልባን ሲኾን ይህም በጸሎተ ሐሙስ ቀን የሚዘጋጅ የተቀቀለ ንፍሮ እንደኾነ አስረድተዋል። ይህም እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ ከንጉሥ ፈርዖን ለመሸሽ ስለቸኮሉ ያልቦካ ቂጣ፣ እርሾ የሌለበት እንጀራ እና የተቀቀለ ንፍሮ በችኮላ አዘጋጅተው በልተው ስለነበር ጉልባን ያንን የመከራ እና የችኮላ ጊዜ የሚታሰብበት እንደኾነም ተናግረዋል።
ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ የጉልባን ሥርዓት ምሥጢራዊ ትርጉም አለው ይላሉ። ጉልባን ሲዘጋጅ ባቄላው ተከክቶ እና ገለባው ከላዩ ላይ ተነስቶለት ሲኾን ስንዴው ደግሞ ሳይከካ ሁለቱም ይደባለቃሉ፤ ከዚህም በላይ በዛ ያለ ጨው ይጨመርበታል ነው ያሉት።
መምህር ዘላለም እንደሚሉት፣ የባቄላው መከካት እና የሽፋኑ መገፈፍ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ልብሱን ገፈው በተለያየ ኹኔታ መግረፋቸውን፣ መከራ ማጽናታቸውን፣ መድማቱን እና መቁሰሉን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የስንዴው አለመከካት የመለኮት ምሳሌ እንደኾነ ይታሰባል ነው ያሉት። ይህ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ ምንም መከራ ቢደርስበትም በመለኮታዊ ባሕሪው ምንም ዓይነት መከራ እንዳላገኘው የሚገለጽበት ምሳሌ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
ሊቁ ጎርጎሪዎስ “መለኮት ሞተ ታመመ ብለህ የምትናገር ከኾነ የመለኮት ገዳይ አንተ ነህ” ይላል። ስለዚህ ስንዴው የመለኮት ምሳሌ ሲኾን ባቄላው ደግሞ የሥጋው የመድማት፣ እና የመገፈፍ ምሳሌ ነው ብለዋል።
ይህ በአንድ ላይ መኾን ሥጋ እና መለኮት ተዋሕዶ መለኮት በሥጋ መከራ መቀበሉን የሚዘከርበት ስለመኾኑም አስረድተዋል።
መምህሩ ጉልባን ሲቀቀል በዛ ያለ ጨው የሚጨመርበት ምክንያት ጨው የበዛበትን መመገብ ውኃ ስለሚያሰጠማ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃ መጠማቱ የሚታሰብበት እንደኾነም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን