የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ።

22

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኀላፊ አበበ ውቤ በመልዕክታቸው ከፌዴራል መንግሥት፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክሉ የጸጥታ መዋቅር እና ከሰፊው ሕዝብ ጋር እጅ እና ጓንት ኾኖ በመሥራት በአማራ ክልል አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር ወጥቶ ወደ ልማት ሥራ ገብቷል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ ለማሳያነት የባሕር ዳር፣ የጎንደር፣ የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞችን የኮሪደር የልማት ሥራዎችን ጠቅሰዋል። በላሊበላ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘውን የልማት ሥራም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ከጸጥታ ሥራው ጎን ለጎን የሕዝብ ግንኙነት ሥራው በተረጋጋ ሁኔታ እየተከናወነ መኾኑም ሌላው ለሰላም መስፈኑ አብነቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ መዋቅሩ አስቀድሞ በማቀድ፣ ከፈጻሚ አካላት ጋር በመወያየት እና በመግባባት ወደ ሥራ መግባቱን ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲከበርም የጸጥታ መዋቅሩን መላው የክልሉ ሕዝብ መደገፍ እና መተባበር እንዳለበት ረዳት ኮሚሽነር አበበ አስገንዝበዋል፡፡

ሕዝቡ ሲገበያይ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ እና ሲመጣ፣ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲመለስ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ሕገ ወጥ ግብይት እንዳይከናወን ሁሉም ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል ረዳት ኮሚሽነር አበበ።

ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ ከታሪፍ በላይ ክፍያ እንዳይኖር፣ ከመጠን በላይ ሰው እንዳይሳፈር እና ሕገ ወጥ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይኖር የትራፊክ ፖሊሶች እና የመንገድ ደኅንነት ባለሙያዎች ከመቼውም ቀናት በተለየ ኹኔታ እንደሚቆጣጠሩ አስረድተዋል፡፡

በግብይት ወቅት ሀሰተኛ የብር ኖት ዝውውር ሊኖር ስለሚችል ማኅበረሰቡም በትኩረት ራሱን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቅም ረዳት ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

ሕዝቡ አጠራጣሪ እና ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጸም ሲመለከት መረጃ ለጸጥታ ኀይሉ በመስጠት የወንጀል መከላከሉን ተግባር እንዲደግፍም ረዳት ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አካባቢያቸውን መጠበቅ በሚችሉበት ኹኔታ መግባባት መደረሱንም ነው የተናገሩት።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኀላፊ አበበ ውቤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወዲሁ መልካም የትንሳኤ በዓል ተመኝተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ጥገና እያካሄደ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next articleየመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ።