
ደሴ: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት 3ኛ ዙር የትምህርት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። የመምህር አካለ ወልድ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ወንዳንተ ደምሴ በትምህርት ቤቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከርቀት የሚመጡ ተማሪዎች ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ በሚያጋጥማቸው ችግር የትምህርት ገበታቸው ላይ በሰዓቱ ለመገኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል። የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የተማሪዎችን ውጤት ከፍ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የካራ ጉቱ፣ የሆጤና መርከዘል ቡርሀን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጉድኝት ሱፐር ቫይዘር ግርማ መኮነን ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ግብዓቶች ቢያሟሉ ተማሪዎች በሚቀርባቸው አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደሚማሩ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ የተሻለ የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት እና ግብዓት ከማሟላት አኳያ የተለያዩ ሥራዎች መሥራታቸውን ተናግረዋል።
ከአጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ ከ122 ሚሊዮን ብር በላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ግንባታ እና ጥገና እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ግንባታዎቹ በዚህ በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቁ እና በ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ትምህርት ለሀገር እድገት እና ብልጽግና አይተኬ ሚና አለው ብለዋል።
ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በቀጣይም በደሴ ከተማ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ መምህራን፣ የትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችን እና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን