ኢየሱስ ክርስቶስ ታላላቅ ተግባራትን የፈጸመባት ዕለት!

28

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሙነ ሕማማት የሚውለው ጸሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ባለ ብዙ ምስጢር እና ባለ ብዙ ስያሜ ነው። በቤተክርስቲያኗ ከሚከበሩ ዕለታት መካከል አንዱ ሲሆን የመከበሩም ምስጢር ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ ታላላቅ ተግባራትን የፈጸመበት ስለኾነ ነው ይላሉ በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባዔ አዳሪ ትምህርት ቤት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙዔል አስናቀ።

ስለ ጸሎተ ሐሙስ ማብራሪያ የሰጡን ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል ”በተለይም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሰጠበት ዕለት በመኾኑ በምዕመናን ልቡ እና የማይዘነጋ ድንቅ ቀን ኾኗል” ነው ያሉት። በዕለቱ በርካታ ቁልፍ እና ለመንፈሳዊ ሕይወት መሠረት የኾኑ ክስተቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ሊቁ ምስጢረ ቁርባን፣ የእግር እጥበት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎት እና የይሁዳ ክህደት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

👉 ምስጢረ ቁርባን

ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህም ደሜ ነው ብሎ ምስጢረ ቁርባንን የገለጠው በዚህ ዕለት ነው። ይህ ድርጊት በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል ያለውን አዲስ ቃል ኪዳን ያመለክታል። ስለዚህ ጸሎተ ሐሙስ እግዚአብሔር የሐዲስ ኪዳንን መስዋዕት የገለጠበት፣ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ፈርሶ የነበረው ኪዳን የታደሰበት በዓል ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በምሴተ ሐሙስ የተጀመረውን የቅዱስ ቁርባንን ጥልቅ ምሥጢር በተመለከተ ሲያብራራ ክርስቶስ ወደ መስቀል ከመቅረቡ በፊት ራሱን ያቀረበበት ምስጢራዊ ማዕድ በማለት ጠርቶታል። በዚህም መሠረት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምስጢራዊ ማዕድ ሲለው ዕለቲቱንም የምስጢር ዕለት ብሏታል። (ማቴ 26 26)

👉 ሕጽበተ እግር (የእግር አጠባ)

ልዑል አምላክ ክርስቶስ ትኁታን ደቀመዛሙርቱን ዝቅ ብሎ ያጠበበት እና ትኅትናን ያስተማረበት ስለኾነ የትኅትና ዕለት፤ የትኅትና በዓልም ይባላል፤ “ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ” ብሎ እንደገለጠው። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ዕለት ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ተነሥቶ የሚክደውን ይሁዳን እንኳን ሳይንቅ ሁላቸውንም አጥቧቸዋል። ይህ ትኅትና መጠን እና ወደር የሌለው ትኅትና ነው። ስለዚህ ይህ ዕለት ልዑል አምላክ ትኁታን አገልጋዮቹን ያጠበበት ዕለት ዕየተባለ ይታወሳል።

👉 የጌታ ጸሎት

በዚህ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ጊዜ ሲጸልይ ታይቷል። የመጀመሪያው የመባረክ ጸሎት ነው። ኅብስቱን ወደ ክቡር ሥጋው፤ ወይኑን ወደ ቅዱስ ደሙ ለመቀየር የጸለየው ጸሎት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በጌቴሴማኒ ስለ ሰዎች የሚቀበለውን መራራ ጽዋ፣ የሚከፍለውን ዋጋ አስመልክቶ ሰዎች እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ለማስረዳት የጸለየው ጸሎት ነው። (ማቴ 26 36)

👉ክህደተ ይሁዳ (የይሁዳ ክህደት)

ሌላኛው በዕለቱ የሚታሰበው ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን መካዱ እና ጌታም በክፉዎች እጅ መያዙ ነው። በነቢያት ቀድሞ ባናገረው መሠረት ጌታ በዕለተ ሐሙስ በአይሁድ እጅ ተይዟል። መያዙ ግን ኃይል አጥቶ አይሁድ ተበረታተውበት አይደለም። ክርስቶስ የተያዘው በኃይል ያለመሆኑን ማንን ትሻላችሁ? ብሎአቸው ክርስቶስን እንሻለን ብለው ሲመልሱ “እኔ ነኝ” ብሎ በመናገሩ ብቻ አይሁድ ኃይል አጥተው መውደቃቸው የክርስቶስን የኃይሉን ጽናት እና የእነርሱን ኃይል ደካማነት አጉልቶ የሚያሳይ እንደነበር ተገልጧል።

👉የጸሎተ ሐሙስ በዓል አከባበር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት መሠረት ጸሎተ ሐሙስ በቤተክርስቲያን ለዕለቱ በተዘጋጀው ምንባብ እና ዜማ በመጨረሻም ከወትሮው ቅዳሴ በተለየው የቅዳሴ ሥርዓት እንደሚታሰብ ሊቀ ሊቃውንት ገልጸዋል። በዓሉን የሚያስታውስ የአመጋገብ ሥርዓት ጎልቶ እንደሚታይም ጠቅሰዋል።

👉ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ እና ገብስ ወይም ስንዴ የሚዘጋጅ በዕለተ ሐሙስ ምዕመናን የሚመገቡት ትውፊታዊ ምግብ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ምሳሌ ያለው ነው። የመጀመሪያው እስራኤል ለጉዞ የቋጠሩት ንፍሮ ምሳሌ ሲሆን ሁለተኛው ሐዋርያት ከሐሙስ ጀምረው ጌታ እስከሚነሳበት እስከ እሑድ ለመጾም አስበው ጥራጥሬ ይሻለናል ብለው ተመግበው ስለነበር ያንን የሚያስታውስ ትውፊታዊ ምግብ ነው።

👉ትውልዱ ከኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎተ ሐሙስ ሥራዎች ምን ይማራል?

ዕለቱ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ እርሱ የባሪያዎቹን እግር ዝቅ ብሎ ያጠበበት፣ ትኅትናን እና ገርነትን ለዓለም ያስተማረበት ነው። ነገር ግን የጌታ ትኅትና የወዳጆቹን እግር በማጠብ ብቻ ያበቃ አልነበረም። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚቀበለው መከራ ሁሉ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳንም ዝቅ ብሎ እግሩን ያጠበበት ትኅትናና ፍቅር የክርስቶስ ብቸኛ መንገዶች መሆናቸው የታየበት ድንቅ ዕለት ነው።

በዚህ ዕለት ክርስቶስ ወደ እርሱ የሚያቀርባቸውን እያሳየ ከእርሱ ከሚያርቃቸውን እንዲርቁ በተግባር ያስተምር ነበር። በዕለቱ ክርስቶስ ሰዎች ከጠብ እና ከጥላቻ እንዲርቁ ለይሁዳ ባደረገው መክሯል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ፦

👉 ስለ ራስ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎች መኖርን፣

👉 ጠላትን ጭምር መውደድን፣

👉 ከትዕቢትና ከተንኮል መራቅን አስተምሯል።

በመኾኑም በዓሉን ስናከብር ማንንም የማይጠላ እርሱን እያሰብን በልቡናችን ያለውን ጥላቻ ልናርቅ፤

ጠላቱ ይሁዳን ወዳጄ ብሎ የጠራው እርሱን በማሰብ ጠላቶቻችንን በመውደድ፤ ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበ እርሱን በማሰብ ታናናሾቻችንን በማክበር ልናስበው ይገባል ብለዋል ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት!
Next articleየትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ጥገና እያካሄደ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡