
ባሕርዳር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን በዋልያ ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በሚገኘው ብርቅየ እንስሳ በዋልያ ላይ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞችን በአጭር ጊዜ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለዞኑ ብቻ ሳይኾን ለሀገር ትልቅ ሀብት እንደኾነም ገልጸዋል። ባለፉት ዘመናት በመንግሥት እና በሕዝቡ የተቀናጀ ጥበቃና ክብካቤ የብዙ ብርቅየ እንስሳት እና እጽዋት መገኛ ማእከል እንዲኾን በመደረጉ በዩኔስኮ መመዝገቡን አስታውሰዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንደኾነም ገልጸዋል ።
ፓርኩ በተደጋጋሚ በሚደርስበት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንደቆየ የገለጹት አሥተባባሪው በተሠራው ጠንካራ ሥራ ከአደጋ መዝገብ ማስወጣት ተችሏል ብለዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የወለደው ሕገ ወጥነት አሁንም ፓርኩን እየፈተነው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚያዝያ 6/2017 ዓ.ም ጃናሞራ ወረዳ ባርና ጎጥ ላይ የፓርኩ ብርቅየ አንስሳ በሆነው ዋልያ ላይ የተፈጸመው ግድያም እጅግ አስነዋሪ የሥርዓት አልበኝነት ጥግ እንደኾነም ገልጸዋል።
ያልተያዙ ወንጀለኞችን ለመያዝ በከባቢው ያለ የጸጥታ ኀይል ጥብቅ ስምሪት ተሰጥቶት በመከታተል ላይ እንደኾነም አመላክተዋል።
ከሰሜን ጎንደር ዞን ኮምዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በፓርኩ ዙሪያ ያለው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት መዋቅር ፓርኩን እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
የዞኑ ልዩ መገለጫ፣ የዓለም እና የሀገር ሃብት መኾኑን በመረዳት ከሚደርስበት ማንኛውም ጥቃት በኀላፊነት መንፈስ መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ወንጀለኞችንም በማጋለጥ ሕዝባዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን