
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕማማት ከሆሳዕና ዋዜማ ቅዳሜ እስከ ትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያጠቃልል ነው። ይህ ሳምንት አዳም አትብላ የተባለውን ዕጸ በለስ በልቶ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ያሳለፈው 5 ሺህ 500 የፍዳ ዘመን የሚታወስበት እንደኾነ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ይገልጻል፡፡
ከሰኞ እስከ ትንሳኤ ዋዜማ ያሉት ስድስቱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታትም ትርጉም ተሰጥቷቸው ይታሰባሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ምስጢራት የተገለጡባት ጸሎተ ሐሙስ አንዷ ናት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትርጓሜ መምህር ኤፍሬም ምናለ እንዳሉት ጸሎተ ሐሙስ የተለያዩ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን የተፈጸመባት እጅግ የተለየች ቀን ናት ብለዋል፡፡ መምህር ኤፍሬም እንዳሉት የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋህደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥ እና ለአርዓያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን በመኾኑ “ጸሎተ ሐሙስ” ይባላል ነው ያሉት።
ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የዓለምን ሁሉ ኃጢዓት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና እና የቅድስና አምላክ በመኾኑ “ሕጽበተ ሐሙስ” እየተባለም ይጠራል ብለዋል።
ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ የኾነው ምሥጢረ ቁርባን የተመሠረተበት ቀንም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስቱን እና ጽዋውን አንስቶ “ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ስጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈሰው ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው ልጅ፤ የሰው ልጅ ደግሞ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ የሚኾኑበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን ነው ብለዋል መምህር ኤፍሬም።
በዚህ ዕለት ክርስቲያን የኾነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል ነው ያሉት፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጾ፤ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ዕለቱ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ እየተባለም ይጠራል ብለዋል።
ዕለቱም ለኃጢዓት እና ለዲያቢሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት የነጻነት ቀን ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ” በማለት የሰው ልጅ ከባርነት የወጣበትን ልጅች የተባለበትን ቀን የሚታሰብበት በመኾኑ ሊቃውንቱ “የነጻነት ሐሙስ” ይሉታል ነው ያሉት።
እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢዓት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይዎቱን መምራት ይኖርባታል፤ ባሮች ሳይኾን ወዳጆች ብሎ ክርስቶስ ጠርቷልና ብለዋል መምህሩ፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን