
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከስሙነ ሕማማት ቀናት ጸሎተ ሐሙስ ብዙ ምስጢር የታየባት ዕለት ናት። ከተፈጸሙት ምስጢራት ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋሪያቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት መኾኗ በቀዳሚነት ይነሳል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢዓት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና እና የቅድስና አምላክ በመኾኑ ዕለቷ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› እየተባለች ትጠራለች።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋሪያቱን እግር በማጠብ ምስጢረ ትሕትናን አሳይቷል፤ ጥበብ እና ፍቅርንም አስተምሯል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የትርጓሜ መምህር ኤፍሬም ምናለ ጸሎተ ሐሙስ ብዙ ታምር የተከናወነባት ዕለት ናት አሉን። በቅዱስ ዮሃንስ ሲጠመቅ የታየው ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ደግሞ ዓለምን በእጁ ሲያጠምቅ ታይቷል።
በዕለት ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋሪያቱ ያደረገውን ለማሰብ ካህናት በቤተክርስቲያን በመገኘት ሕጽበተ እግር ያከናውናሉ። በወቅቱ የሚያጥበው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ፣ የሚታጠቡት ደግሞ የሐዋሪያት ምሳሌዎች ናቸው። ሕጽበተ ሥርዓቱ ሃይማኖታዊ ባሕል ኾኖ የሚከናወን ነው። አማኙ ይህን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በማከናወኑ ሰማያዊ በረከት እና ምድራዊ ጸጋን ያገኝበታል፤ ለሥጋወ ደሙም ያበቃዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን በትህትና ዝቅ ብሎ እንዳጠበው አማኙም ትህተናን፣ ፍቅርን እና መከባበርን ሊማር ያስፈልጋል። አማኙ በቤተክርስቲያን ተገኝቶ በጾም በጸሎት ማሳለፍ እና ከሰማያዊ በረከቱ ተካፋይ መኾንም ይገባዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ፈለገ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም አገልጋይ እና የቅኔ እና የቅዳሴ መምህር ሄኖክ አሸናፊ እንዳሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያቱ ለሰዎች እንዲያደርጉ ያስተላለፈውን የማይሻር አምላካዊ ትዕዛዝ ለማስታወስ ዛሬ ላይም ካህናት በቤተክርስቲያን በመገኘት ሕጽበተ እግር ያከናውናሉ።
ሥርዓቱ ከመከናወኑ በፊት ‹ጸሎተ አኩቴት› ወይንም “የምሥጋና ጸሎት” በአባቶች ይከናወናል ነው ያሉት። ጸሎቱ ከተከናወነ በኋላ የሕጽበት ሰዓቱ ሲደርስ ውኃው ተባርኮ አባቶች እንደየ ኀላፊነታቸው የበታቾቻቸውን እግር እንደሚያጥቡም አስረድተዋል። ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት ደግሞ የወይራ እና የወይን ቅጠል ጥቅም ላይ ይውላሉ ነው ያሉት።
ምሥጢሩም ደግሞ ወይራ ጽኑ ወይንም ጠንካራ በመኾኑ ክርስቶስ መከራ መቀበሉን፣ እግር የሚያጥቡት አባቶች እና የሚታጠቡት አማኞች ደግሞ መከራ ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውን ለማሳየት እንደኾነም ጠቅሰዋል። የወይን ቅጠሉ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በወይን የተመሰለ መድኃኒት መኾኑን ለመግለጽ ነው ብለዋል።
ደሙን አፍስሶ ለአማኙ የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለመዘከር ታሳቢ ተደርጎ በመስጠቱ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን