ግጭቱ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን ለከፋ ችግር ዳርጓል።

16

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሴቶች ማኀበር እና ዩኒሴፍ በምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞን ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መከላከል እና ምላሽ ፕሮጀክት ላይ የትብብር ግምገማ አካሂዷል።

የአማራ ሴቶች ማኀበር (አሴማ) ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር በምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል እና ምላሽ መስጠት ፕሮጀክት ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።

የአማራ ሴቶች ማኀበር ኀላፊ ገነት ወንድሙ ማኀበሩ ግንቦት 27/1990 ዓ.ም በክልሉ እና በሀገሪቱ ያለውን የተዛባ የሥርዓተ ፆታ አስተሳሰብ እና ተግባር ለማስወገድ የተቋቋመ ነው። በክልሉ የሚገኙ ሴቶች መብት እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በመልካም አሥተዳደር እና በፖለቲካው ዘርፍ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ እና ትግል ለማድረግ የተቋቋመ ማኅበርም ስለመኾኑም አስረድተዋል።

ማኀበሩ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አባላት ያሉት ሲኾን እስከ ቀበሌ በመውረድ ለሥራው መቃናት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ 32 ሺህ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉትም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ተጋላጭ ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሀብቶችን በመፈለግ በተገቢው ቦታ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ኀላፊዋ የጠቆሙት።

በዚህም በዩኒሴፍ በሚደረገው ድጋፍ በጎጃም ቀጣና በ4 ዞኖች በ10 ወረዳዎች ተልዕኳቸውን እየተወጡ መኾኑንም ተናግረዋል። በወረዳዎቹ የሴቶች እና የልጃገረዶች ምቹ ማረፊያ ክፍል ከነሙሉ ቁሳቁሱ በማሟላት ሴቶች የተለያዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ እና ሐሳብ እንዲለዋወጡ መደረጉንም አብራርተዋል።

በእነዚህ ማዕከላት የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ውይይት ይደረጋል፤ ጾታን መሠረት ያደረገ ምላሽ የመስጠት ተግባራት ይከናወናሉ። በሕይወት ክህሎት ውይይትም መፍትሔ ይሰጣል፤ የግል የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት ይሰጣል፣ እንዲኹም የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ልምምድ ይደረጋል ነው ያሉት።

እነዚህ የሴቶች ምቹ ማረፊያዎች በአብዛኛው በሀገራዊ ቀውሱ ምክንያት ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ናቸው።

በተለያየ መንገድ የጉዳት ሰለባ የኾኑ ሴቶች ከጉዳታቸው የሚያገግሙበት እና የሚድኑበት ብቻ ሳይኾን በሚሠሩት የእጅ ሥራ የሙያ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ተግባርም ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶችን እያስተናገደ የቆየ ክልል በመኾኑ በዛ ያለ የማኅበረሰብ ክፍል በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ከሌሎች በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ኾኖ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች እና የሲቪክ ማኅበራት ጉዳዩን በጋራ በመሥራት እልባት ሊሰጡት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር”
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቬይትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት በመቀጠል ከቬይትናም ፕሬዝዳንት ክቡር ጄነራል ሉዎንግ ኩዎንግ እና ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር ትራን ታንህ ማን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።