
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የሚያከናውናቸውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎች በ11 ክልሎች እና 2 የከተማ አሥተዳደሮች ማከናወኑ አንስቷል። በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ የክልል እና ከተማ አሥተዳደር ባለድርሻ አካላት መሰብሰብ ተቀዳሚ ግቡ መኾኑ ቢታወቅም ሂደቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ቀጥተኛ ያልሆነ በጎ አስተዋፅኦን በማበርከት ላይ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ቀጥለው የቀረቡት ሀሳቦች ኮሚሽኑ በሂደቱ እያስመዘገባቸው ያሉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶች ናቸው፡፡
1. በባለድርሻ አካላት መካከል የተሻለ መተማመን እና ግንኙነትን ማዳበር
እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡ ውይይቶቹ በተለያየ ፈርጆች በተለዩ ወገኖቻችን መካከል መተማመንን በመገንባት ተስፋ ሰጪ የሆኑ በጋራ የመሥራት ልምምዶች እንዲዳብሩ አስችለዋል፡፡
2. የባለድርሻ አካላት ባለቤትነትን መፍጠር
የሀገራዊ ምክክር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባለቤትነት ተሰምቷቸው በሂደቱ በእኩል ሊሳተፉበት የሚገባ የዲሞክራሲ ሂደት ነው፡፡ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በተከናወነባቸው የሀገራችን አካባቢዎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ ስኬት በተለያየ ረገድ ያሳዩት ርብርብ እና ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ይህም በሂደቱ ያላቸውን ባለቤትነት እንዲገነቡ አስችሏቸዋል፡፡
3. የዲሞክራሲ ባሕልን ማሳደግ ሀገራዊ ምክክር ከተደረገባቸው አብዛኛዎቹ ሀገራት ማስተዋል የሚቻለው ሂደቱን አካታችና አሳታፊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
ይህም መሠረታዊ ከሆነው የዲሞክራሲ አስተምህሮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በመግለፅ፣ ወኪሎቻቸውን በመምረጥ፣ ውሳኔዎችን በመስጠት እና በሂደቱ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው እንዳስቻለ መዛግብትም ያስረዳሉ፡፡
በዚሁ አግባብ በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሲሳተፉ የቆዩ የባለድርሻ አካላት ወኪሎችም ከላይ የተጠቀሱትን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ የተገበሩ ሲሆን ይህም ዲሞክራሲን እንደ ባሕል ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡
4. የምክክር ባህልን ማጎልበት የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶችን ሀገር በቀል በሆኑ መንገዶች መፍታት የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓት ያልተፈቱ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ሂደቱ ሀሳቦች በሚገባ እንዲንሸራሸሩ መንገዱን አመቻችቷል፡፡ ይህም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ጎራዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ላይ ተወያይተው የምክክርን ባሕል እንዲያጎለብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
5. መረጃዎችን ማሰባሰብ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉ እሙን ነው፡፡ በሂደቱ ኮሚሽኑ ለስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ፍጆታ የሚውሉ እና በቀጣይ ለሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማደራጀት ስኬታማ የሆኑ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!