
ጎንደር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “አገልግሎት አሰጣጤን በማሻሻል፣ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ከተማዬን እክሳለሁ” በሚል መሪ መልዕክት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች እና ከተቋማት ቡድን መሪዎች ጋር በጎንደር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በሀገር ግንባታ ትልቅ ቦታ ያለው የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝብን በማገልገል ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
“የሁሉም ሥራዎች ቁልፍ የኾነው የአገልግሎት አሠጣጥ በተገቢው መንገድ ከተሠራበት ሰላም እና ልማትን ማረጋገጥ ይቻላል” ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት የመንግሥት ሠራተኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲሠጡ አቅማውን ለማጎልበት እንደሚሠራም ገልጸዋል። የተጀመሩ የልማት ዕድሎችን ለማስቀጠል እና ውጤታማ ለማድረግ አገልግሎት አሠጣጡን ማሻሻል እንደሚገባም አመላክተዋል።
በቀጣይ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እውን እንዲኾኑ የመንግሥት ሠራተኚች ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የጠቀሱት አቶ ይርጋ አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣን እና ቀልጣፋ ከኾነ የጎንደርም ኾነ የክልሉ ዕድገት ይረጋገጣል ብለዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የመንግሥት ሠራተኞች ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት በከተማው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማሳካት ማገዝ እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ልማቱን ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ በመኾኑን ገልጸዋል። የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ ሰላምን ለማረጋገጥ የአገልግሎት መጓደሎችን ማስተካከል አለባቸው ነው ያሉት። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን የከተማ አሥተዳደሩን አገልግሎት አሰጣጥ በጥንካሬ እና በድክመት የተመለከተ ሰነድ ለውይይቱ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የሕዝብ አገልጋይነት ስሜትን በመላበስ ብልሹ አሠራርን በመታገል ማስተካከል እንደሚገባቸውም አብራርተዋል። የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ውጤታማ በኾነ መንገድ መፈጸም እና ማስፈጸም እንደሚገባም አሳስበዋል። ከሕዝቡ ግብዓት በመሠብሠብ እና ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እንደሚሠራም ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
