
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ የሥልጣን ርክክብ ከተደረገ በኋላ የለውጡ መንግሥት የመጀመሪያውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምን ጨምሮ በርካታ ማሻሻያዎችን ሲያካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለውጡን ተከትሎ ኢኮኖሚው ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ተቋቁሞ 8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ባካሄደው የስንዴ ልማት ተግባር ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደኾነ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የማይታረሱ መሬቶችን ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ መልማቱን ተናግረዋል። መደበኛውን ዝናብ እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የተጀመረበት ሂደት ፈጣን ነው ብለዋል።
በግሪን ኢኒሼቲቭም ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ 40 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዉ የደን ሽፋንን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት የእንሰሳት ሀብት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለማልማት መንግሥት በሰጠዉ ልዩ ትኩረት በባለፉት ወራት ከፍተኛ የኾነ ለውጥ ማምጣት የተቻለበት ነው ብለዋል፡፡
በተለይ መንግሥት በአሁኑ ወቅት እየወሰደ ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሁሉም መስክ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ መኾኑን አንስተዋል። መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የፖሊሲ እና የሪፎርም እርምጃዎች በትክክለኛ ጎዳና ላይ መኾናቸውን የሚያመላክት ውጤት እየተገኘ መኾኑን ገልጸዋል።
የዋጋ ግሽበት የሚጨምርበት ምጣኔ እየቀነሰ መሄዱ፣ የውጭ ምንዛሬ በገበያ መመራቱ እና የመጠባበቂያ ክምችት እየጨመረ መኾኑ፣ ተጨባጭ ማሳያዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ፣ እንደምታ እና ለሀገሪቱ ምን ጥቅም እና ጉዳት ሊኖረው ይችላል የሚለውን ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ ለማስመዝገብ ያቀደችውን የ8 ነጥብ 4 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳካት የሁሉን ርብርብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
