
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ ለሚገኙ የኑሮ ጫና ላለባቸው እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማዕድ ማጋራት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።
የማዕድ ማጋራቱ መርሐ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት 5 ሺህ ለሚኾኑ ነዋሪዎች የተካሄደ ሲኾን በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ደግሞ 200 ሺህ የሚኾኑ ሰዎች ተጠቃሚ ኾነዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማዕድ ማጋራት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአሥተዳደሩን ፍቅር እና አክብሮት የሚገልጽ አንዱ የሥራው አካል እንደኾነ ገልጸዋል።
ይህ ተግባር የእርስ በርስ መተሳሰብን፣ መከባበርን እና መዋደድን የሚያዳብር ከመኾኑም በላይ፣ እንደ ሀገር እየተተገበረ የሚገኘውን የሰው ተኮር እሳቤን አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
“መስጠት አያጎድልም” ያሉት ከንቲባዋ የከተማ አሥተዳደሩ ማዕድ ሲያጋራ ሁልጊዜ ከጎኑ የሚቆሙትን ባለሃብቶች፣ ተቋማት እና ወጣት በጎ ፈቃደኞችን አመሥግነዋል። እንዲህ አይነት ሰው ተኮር የኾኑ መልካም ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በማዕድ ማጋራቱ ሥነ ሥርዓት ድጋፍ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የከተማ አሥተዳደሩ በዓሉን ሳይቸገሩ በደስታ እንዲያሳልፉ ላደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ለዜጎቹ ደኅንነት እና ማኅበራዊ ተሳትፎ ያለውን ትኩረት የሚያሳይ ተግባር እንደኾነ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
