
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሟል። በግምገማው የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኃይሌ አበበ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ113 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወጭ መቆጠቡን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከውጭ የሚገቡ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ በመተካት 52 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ ለማስቀረት ታቅዶ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል። በተሥራው ሥራም 113 ሚሊዮን 117ሺህ 736 የአሜሪካን ዶላር በማዳን ከዕቅዱ በላይ ስኬት ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በውጭ ምንዛሬ ገቢ ቢሮው 18ሺህ 779 ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናትን ወደ ውጭ በመላክ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ መሥራቱን አብራርተዋል። በተሠራው ሥራም 8 ሺህ 768 ኪሎ ግራም በመላክ ከ9 ሚሊዮን 34 ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል። ገቢው የተገኘው ከወርቅ እና ከኦፓል ምርት መኾኑም ተመላክቷል።
በማዕድን ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ ለ34 ሺህ 386 ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ31 ሺህ 136 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ የወጣቶች ድርሻ 82 ነጥብ 7 በመቶ መኾኑን አመላክተዋል።
ከአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የተቋሙን አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኀላፊው በቀጣይ ወራት ሁሉም መሪ እና ሠራተኛ ውጤታማ ሥራ የሚሠሩበት ተቋም ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
