
ከአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ሁለቱ መሪዎችና የልኡካን ቡድኖቻቸው የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል። በሁለቱ ሀገራት የተካሄዱ ማሻሻያዎችን እንዲኹም ለትብበር የሚኾኑ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለይም የልምድ ልውውጥን እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
መሪዎቹ የትብብር ሰነዶችን የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይም ተገኝተዋል። በንግድ እና በትምህርት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ መንገድ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተደርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቬትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የመንግሥት መሪ ያደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የኦፊሴላዊ ጉብኝት መኾኑን የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
