“አልማ ተባብሮ የመሥራት እና ሕዝብን ከሕዝብ የማስተሳሰር ትልቅ አቅም ያለው ተቋም ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

38

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ እና የአልማ ጠቅላላ ጉባኤ ሠብሣቢ ፋንቱ ተስፍዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ፣ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ እና የአልማ ሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ እና የአልማ ጠቅላላ ጉባኤ ሠብሣቢ ፋንቱ ተስፋዬ “አልማ ተባብሮ የመሥራት እና ሕዝብን ከሕዝብ የማስተሳሰር ትልቅ አቅም ያለው ተቋም ነው” ብለዋል። ሁሉም የልማት ድርጅቶች ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸውም ልምድ የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል።

ከአማራ ክልልም አልፎ አጎራባች ክልሎችን እና መላ ኢትዮጵያውያንን ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ከልማት ተቋማት ይጠበቃል ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያንን አስቦ መሥራት ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲመጣ ጉልበት ይኾናል ብለዋል።

አልማ በእቅድ የያዛቸውን ሥራዎች በአግባቡ ሲፈጽም እንደቆየ ገምግመናል ያሉት አፈጉባዔዋ የተግባር ሥራዎችም በአካል የሚታዩ ናቸው ነው ያሉት። ማኅበሩ ዕውቀት እና ልምድ እያዳበረ የመጣ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል። ልምድ እና ቁርጠኝነት ሥራዎችን ለመፈጸም ትልቅ ግብዓት እንደኾነውም አብራርተዋል።

ማኅበሩ ለወደፊትም የክልሉን ነባራዊ ኹኔታዎች ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን እንዲያከናውንም አሳስበዋል። በተለይም ትምህርት ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል። ማኅበሩ ትምህርት የሕዝባችን ዋና መሻገሪያ መንገድ መኾኑን በመረዳት አቅዶ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል፤ ከግንባታ ባሻገርም የትምህርት ቤቶችን ቁሳቁስ ማሟላት እና ተማሪዎችን ተወዳዳሪ ማድረግ ከአልማ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው ብለዋል።

ሕዝቡም ከአልማ ጎን በመኾን እና በመደገፍ ችግር የገጠመውን የትምህርት ሥራ መልሶ በጋራ መጠገን እንደሚገባው መልእክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየከተማዋን ገጽታ በአዎንታ ሊቀይሩ የሚችሉ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው።
Next articleየቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋዊ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት አድርገዋል።