አብሮ ያላመሸ ባለጠጋነትን የማግኘት ተስፋ …፡፡

282

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ወይዘሮ ሰቨን ላኩ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዝቋላ ወረዳ ሰሜን በር ቀበሌ ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ የ70 ዓመቷ አዛውንት ‘‘የዛሬን አያድርገውና ሦስት የፍየል እረኞች፤ ሁለት ገበሬዎችን የምናስቀጥር ባለፀጋ ነበርን’’ ይላሉ፡፡ ለእርሳቸው የእንስሳት ብዛት የሀብት መገለጫቸው ነው፡፡ በጥምር አርሶ እና አርብቶ አደርነት የሚተዳደሩት ወይዘሮ ሰቨን የ1977ዓ.ም ድርቅን የሚያስታውሱት በብዙ ሰዎች አንደበት ውስጥ መኖሩን እንጂ ለጎጆቸው ፈታኝነት አልነበረውም፡፡ ሀብታቸው ከባለፉት 15 ዓመታት በኋላ ግን በተደጋጋሚ በአካባቢው በሚፈጠር የዝናብ እጥረት፣ የተከዜ ሰው ሠራሽ ሐይቅ እንስሳቶቻቸው የሚኖሩበትን አካባቢ በመሸፈኑ የእንስሳት ቁጥራቸው እንደቅጠል እየረገፈ መሄዱን ያስታውሳሉ፡፡

ወተት እና አይቡን፤ ቅቤውና ማሩን ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለእንግዳ እና ለወዳጅ ሁሉ የሚሰጡ ስጦታ እንጂ በገንዘብ የሚለወጥ ፀጋ አድርገው አያስቡም ነበር፡፡ ሰጥተው እና አብልተው የለመዱት እጆች፣ ብዙዎች ከበዋቸው የሚውሏቸው፤ የእንግዳው ማረፊያዋ ወይዘሮ ሰቨን ዛሬ ግን ድህነት ጠፍሮ ይዟቸዋል፡፡ ፈትፍተው ማጉረስ የለመዱት እጆች ፊት በሚነሱ ፊቶች ተተክተውባቸው፤ በሽምግልናቸው ወቅት ‘‘አግኝተህ… አትጣ’’ እያሉ እንዲመርቁም አድርጓቸዋል፡፡ እንስሳቶቻቸው አልቀው ሁለት ሦስት የሚባሉ ሁነዋል፡፡ ያኔ ‘ለዓይን ይከብዳል’ ያስባሉ የፍየሎቻቸው ብዛት ዛሬ ያለጠባቂ በየሰፈሩ አብረዋቸው የሚውሉ በጣት የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡

ሳይሰፍሩ የሰጡት እነዚያ ለጋስ እጆቻቸው ዛሬ የካናዳ ስንዴ እየተሠፈረላቸው ነው፤ ያኔ ማርና ቅቤውን ያለስስት አብልተው የለመዱት ወይዘሮ ዛሬ የአሜሪካን ዘይት ለመሸመት ተገድደዋል፡፡ ‘‘ሀብት ለሰው ልጆች በነጻ የሚሰጡት ጸጋ እንጂ ለተራበ ሰው በሽያጭ የሚያቀርቡት አይደለም’’ ብለው የሚያምኑት አዛውንቷ ይህ ዘመን የእመነታቸውና የኑሯቸው ተቃርኖ ማሳያ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ከምንም በላይ ለመጪው ትውልድ የኑሮ ሂደት እንደሚጨነቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰቨን ‘‘እኛስ አንድ ሰኞ ቀረችን፤ …. በገጠር የሚገኝ የዚህ አካባቢ ትውልድ ተስፋ ግን ያሳስበኛል’’ ይላሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ሰቨን ላኩ ሁሉ ወይዘሮ ንግሥተ ወልዱ በአበርገሌ ወረዳ ሰቀ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን በእንስሳት እርባታ በባለጠግነት ከብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ባለጠግነት ባልተሸጠባቸው ዘመናት ከራሳቸው አልፈው ለበርካቶች የሕይወት መከታ ሆነዋል፡፡ ያፈሯቸውን እንስሳትንም ሆነ የእንስሳት ተዋጽኦ ሁሉም ጋር አብረው ተጋርተው ኑረዋል፡፡ ከጥቂት አስርት ዓመታት ወዲህ ግን ‘‘ድርቁ እየበዛ በመሆኑ አይደለም ከብትና ፍየሉ እንጨቱም እየደረቀብን ነው’’ ይላሉ፡፡ የፍየል በሽታ በወረርሽኝ መልኩ በተከሰተ ቁጥር ሀብታቸውን ማመንመኑን ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሰው ቁጥር መጨመር፣ የግጦሽ ቦታ እጥረት መፈጠር፣ የግጦሽ ቦታዎች ወደ እርሻ መሬቶች መስፋፋት ምክንያት የእንስሳት ሀብታቸው ራሳቸውን እንዳይችሉ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ንግሥተ ‘‘ባለጠግነት በሚሸጥበት በሚለወጥበት ጊዜ እኛ ሀብት አጣን’’ ይላሉ፡፡ የሀብት መገለጫውም ከእንስሳት እርባታ ይልቅ የንግድ ዘርፉ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ‘‘ፊተኞችን ኋለኞች’’ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ለእነ ሰቨን እና ንግሥተ የመሰሉ አርብቶ አደሮች ተስፋን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የማዕከሉ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተመራማሪ አቶ የሺዋስ ዋለ የበግ እና የእንስሳት ማዳቀል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዝቋላና አበርገሌ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ሰባት መንደሮች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርመሩ ‘‘የተሻለች ምርት የምትሰጥ እናት ፍየል በወለደችው ሪማ በመጠቀም ዝሪያ ማሻሻል ነው’’ ብለዋ አቶ የሺዋስ፡፡ የተሻሻሉት የአበርገሌ የፍየልና በግ ዝርያዎቹ ዝናብ በመጣ ወቅት ራሳቸውን ለእርባታ የሚያጋልጡ፤ የተሻለ የወተት ምርት በቀን እስከ 344 ሚሊ ሊትር የሚሰጡ፤ በክብደታቸው በዓመት እስከ 17 ኪሎ ግራም የሚደርሱ፤ በስድስት ወራት ውስጥ ለገበያ የሚቀርቡ እና በስጋ ጣዕማቸው የተለዩ መሆናቸውን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

ምርምሩ በደረሰባቸው ሰባት መንደሮች 432 ሺህ 855 የፍየልና በግ ዝሪያዎች አሉ፤ 217 አርሶ አደሮችም በሥራው ታቅፈው እየሠሩ መሆናቸውን አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡

ተመራማሪው የሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ያዋጣቸውን የተሻሻሉ የፍየልና በግ ዝሪያዎችን ለሁሉም አርብቶ አደሮች እንዲዳረስ የግብርና መምሪያው ኃላፊነት ወስዶ ሥራውን መረከብ እንዳለት በተደጋጋሚ ቢናገሩም አለመሠራቱን አስታውቀዋል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ጥጉየ የሰቆጣ ዝናብ አጠር የምርምር ተቋም ያደረገውን ግኝት ለማስፋት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተያዘው ዓመትም በምርምር የተረጋገጡ 400 አውራዎችን በመግዛት ወደሰቆጣ ወረዳ ለማስፋት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ የምርምሩን ሥራ በባለቤትነት ይዞ ለማስፋት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

በአበርገሌ ወረዳ ሳዝባ ቀበሌ በፍየልና በግ ማርባት ዘርፍ በሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ከታቀፉ አርብቶ አደሮች መካከል አቶ አለፈ ታደሰ አንዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እንስሳቶቻቸው በመኖ እጥረት ይከሱ ስለነበር ገበያ ሲወጡ ዋጋቸው ዝቅተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ወተት የመያዝ አቅማቸውም ዝቅተኛ ስለነበር ከቤተሰብ ፍላጎት አያልፉም ነበር ብለዋል፡፡ በምርምሩ በመታቀፋቸው ግን በዝሪያ ማሻሻል በወተት ምርታቸውና በስጋ ክብደታቸው ከፍተኛ የሆኑ እንስሳትን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የተዳቀሉ በግና ፍየሎችን በስድስት ወራት ውስጥ በጥሩ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ምርምሩ በእንስሳት የሚከሰት በሽታንም በየወቅቱ በመከታተል ስለሚያክም ከዚህ በፊት ይፈጠርባቸው የነበረውን ሞት ሙሉ በሙሉ መቀነስ መቻላቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ይህ ምርምር ዳግም የዋግን የፍየልና በግ እንስሳት ቁጥር በመመለስ ተጠቃሚነትን በአዲስ መልክ እንደሚያረጋግጥላቸው የእነአቶ አለፈ ታደሰ አርብቶ አደር ጎደኞች ቄስ ገብረ ክርስቶስ አዳነ ሁሉ ያምናሉ፡፡ የእነወይዘሮ ሰቨን ላኩን የማታ እንጀራም እንደሚመልስ ተስፋ ተጥሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበባሕር ዳር ሁለት አካባቢዎች በመኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ፤ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
Next articleበኩር ግንቦት 10/2012