
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፈታኝ የኾኑ ተማሪዎችን ለማብቃት በተመረጡ መምህራን ትምህርት እየተሰጠ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት እና ትምህርት መሪዎች ጋር ”ትምህርት ለትውልድ፤ ትምህርት ለጥራት” በሚል መሪ መልዕክት የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ የክልላችን ትምህርት በርካታ ፈተናዎች የገጠሙት ሲኾን ችግሩን የሚፈታው ደግሞ ውይይት ነው ብለዋል፡፡ እንኳን አኹን ክልሉ የሰላም እጦት በገጠመበት ወቅት በሰላሙ ጊዜም የትምህርት ጥራት ችግር እንደ ነበር አስታውሰዋል። አቶ መኳንንት ውስንነቶቹን በሥራ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በግጭት የሚመጣ ልማትም ኾነ ሌላ አዎንታዊ ነገር የለም ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ሁሉም ባለድርሻ አካል ለትምህርት ጥራት ሊረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ክልል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ግብዓት እየተሟላ ስለሚገኝ የትምህርት ጥራት ጥያቄው በመፈታት ላይ ነው ብለዋል አቶ መኳንንት ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) በ2017 የትምህርት ዘመን ከ136 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ 125 ሺህ 661 ተማሪዎች በመማር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የተማሪዎችን የመማሪያ መጻሕፍት ስርጭት በተመለከተ በአንደኛ ደረጃ አንድ መጻሕፍ ለሁለት ተማሪዎች ተሰጥቷልም ብለዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማን ገጽታ የሚመጥን ትምህርት ቤቶች የሏትም ያሉት መምሪያ ኀላፊው የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በአዎንታ መገንባት ተገቢ ነው ብለዋል።
እስካኹን ድረስ 116 ሚሊዮን ብር ፈሰስ በማድረግ የከተማ ገጽታን በአውንታ ሊቀይሩ የሚችሉ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ መምሪያው 24 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግም ትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎች እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ ተፈታኞችን ለማብቃት ትምህርት እየተሰጠ መኾኑንም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
አንደኛው ወሰነ ትምህርት ድረስ በየትምህርት ቤቶች የሚገኙት ቤተ ሙከራዎች ተፋዘው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ መመሪያው ባደረገው ቅኝት የተከሰቱ ችግሮችን በማስተካከል እና ለ200 የሳይንስ መምህራን ትምህርት እና ሥልጠና በመስጠት ተዘግተው የቆዩ ቤተ ሙከራዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማምጣትም ከመደበኛ የትምህርት ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሑድም የማካካሽ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ተማሪዎች የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እያገኙ ነውም ብለዋል፡፡ ጥሩ ውጤትም ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
የቁልቋል ሜዳ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት አገር ነቃጥበብ ትምህርት ቤታቸው 1ሺህ 736 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ እያስተማራቸው የሚገኙትን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎትም እየሰጠ መኾኑን ርእሰ መምህሯ ጠቁመዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
