የተረጋጋ የበዓል ገበያ!

29

ወልድያ: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ ሳምንታዊ የገበያ ቀን በኾነው ዕለተ ማክሰኞ የበዓል ገበያ እንቅስቃሴን አሚኮ ተዘዋውሮ ቃኝቷል። የበዓል ገበያው አንጻራዊ የዋጋ መረጋጋት የታየበት መኾኑንም የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ በሦስቱም ክፍለ ከተሞች የገበያ ድንኳኖችን በመትከል ሁሉንም ዓይነት ምርቶች ነጋዴዎች ለሸማቾች እንዲያቀርቡ መደረጉንም ታዝበናል። ለበዓል አስፈላጊ የኾኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አንጻራዊ የዋጋ ቅናሽ ማሳየታቸውን የወልድያ ከተማ ሸማቾች ተናግረዋል።

ሽንኩርት ቀድሞ ከነበረው በኪሎ 60 ብር ዋጋ በድንኳኖቹ 35 ብር እየተሸጠ መኾኑን ሸማቾች ነግረውናል። አምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይት ከ1ሺህ 600 ብር ዝቅ ብሎ በ1ሺህ 460 ብር እየተሸጠ መኾኑን ነው ያረጋገጥነው። የበግ እና ፍየል ገበያ ዋጋ ካለፉት ወራት ግብይት አኳያ አንጻራዊ ቅናሽ ያሳየ ቢኾንም የእርድ ሰንጋ ዋጋ መወደዱን ግን ሸማቾች ተናግረዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወንድሙ ሕገ ወጥ ግብይትን እና በዓልን ምክንያት ያደረጉ የተለመዱ የዋጋ ንረቶችን በመቆጣጠር የከተማው ነዋሪ በዓሉን በተረጋጋ ኹኔታ እንዲያሳልፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የግብይት ተዋንያን የኾኑ ነጋዴዎችን እና ሸማቾችን በቀጥታ ለማገናኘት በየ ክፍለ ከተሞቹ የገበያ ድንኳኖችን በመትከል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርት እንዲቀርብ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተለይም የንግድ ሕጉን በመጣስ እና በሕገ ወጥ ፈቃድ ሲዘዋወር ተገኝቶ የተወረሰን ሽንኩርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

በመጋዘን ካለው ውጭ ከ450 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ነጋዴዎች ወደ ከተማዋ እንዲያስገቡ በተሠራው የንግድ ትስስር በቂ አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል፤ በዚህም የምግብ ዘይት ዋጋ እንዲቀንስ ኾኗል ብለዋል።

ከዶሮ እና እንቁላል አቅርቦት አኳያም ከእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ጋር በጥምረት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአፍሪካ ኅብረት ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ጥበብ የተሞላበት አመራር መስጠት አለበት” አምባሳደር ኂሩት ዘመነ
Next article“አልማ የመተባበርን እና የአንድነትን ፋይዳ በተግባር ገልጦ ያሳየ ማኅበር ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)