
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ኅብረት የአሥፈጻሚ ምክር ቤት 24 አስቸኳይ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በስብሰባው ላይ በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ኂሩት ዘመነ መልዕክት አሥተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ፣በጂኦፖለቲካ ውጥረቶች፣ግጭትች፣ በብድር እዳ፣ በሰብአዊ ቀውሶች እና ሌሎች አይገመቴ ሁኔታዎች በአኅጉሪቷ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፉ የአፍሪካ ኅብረት ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ በመገንዘብ ጥበብ የተሞላበት አመራር መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል።
እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ኅብረቱ ያስቀመጠው አጀንዳ 2063 ጋር የተናበበ እና አኅጉሪቱን የተረጋጋች እና ዘላቂነት ወደ አለው የእድገት አቅጣጫ የሚመራ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል። ምክር ቤቱ በስብስባው የአንድ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ምርጫ ያካሂዳል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ሕግ አማካሪ አደረጃጀት እና የአፍሪካ የሕዋ ምክር ቤት በተመሳሳይ አንድ አንድ አባላት ያስመርጣሉ።
ምክር ቤቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን፣ የትምህርት፣ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር የምርጫ ሂደት አስመልክቶ የተዘጋጀ ረቂቅ ሪፖርትን ያዳምጣል።
የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚ ምክር ቤት በኅብረቱ አባል ሀገራት የጋራ ፍላጎት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስተባብርና ውሳኔ የሚሰጥ አካል ነው።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍን ጨምሮ ሌሎች መሪዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
