
አዲስ አበባ:ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጠቅላላ ጉባኤው የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አደባባይ ሙሉጌታ፣ የቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን ባለቤት ኢንጂነር ቢጃይ ናይከር፣ የአዲስ አበባ ክፍለከተሞች የአልማ በጎ ፈቃደኛ ሠብሣቢዎች፣ ከድሬዳዋ እና ቤንሻንጉል ክልል አልማ ጽሕፈት ቤት የተገኙ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ጉባኤው እየተካሄደ ያለው “በራስ አቅም የመልማት ምልክት” በሚል መሪ መልዕክት ነው። ጉባኤው ያላፉት ጊዜያትን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የቀጣይ አምሥት ዓመታት ዕቅድን እና የኦዲት ሪፖርትን ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሏል።
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አደባባይ ሙሉጌታ አልማ ሁሉን አቀፍ በኾኑ የሕዝብ የልማት ሥራዎች ላይ የሚሠራ ማኅበር መኾኑን ገልጸዋል። አባላትን በማፍራት፣ ረጂ ድርጅቶችን አስተባብሮ ገቢ በማምጣት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከር የሚያስፈልገው ጊዜ ላይ መኾኑንም ገልጸዋል። ዛሬ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ጨምሮ የልማት ማኅበሩን አቅም ለማሳደግ ሁሉም እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በጉባኤው የተሳተፉት የቢጃይ ኢንዱስትሪያል እና ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን ባለቤት ኢንጂነር ቢጃይ ናይከር ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ከክልሉ እና ከአልማ ጋር አብረን እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
