ለሰኔ ዝግጅት!

36

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ባንተይሁን ዓለም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጓንጓ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ እንዳሉት ያላቸውን ስድስት ተኩል ቃዳ መሬት በስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ እና በቆሎ ለመሸፈን ተዘጋጅተዋል። “ማሣን ደጋግሜ እንዳርስ ባለሙያዎች መክረውኛል” የሚሉት አርሶ አደሩ በተለይ ስንዴ የሚያመርቱበትን ማሣም አራት ጊዜ አርሰው መዝራት እንዳለባቸው የግብርና ባለሙያዎች እንደመከሯቸው ተናግረዋል።

በዚህ መሠረትም አምና ኑግ ዘርተውት የነበረውን ማሣ ዘንድሮ ስንዴ ለመዝራት እስካሁን ሁለት ጊዜ አርሰው ማለስለሳቸውን ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ክረምቱ እንደገባ በማረስ በአራተኛው እርሻ ለመዝራት ከወዲኹ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። አርሶ አደር ባንተይሁን አሲዳማ አፈር የኾነውን መሬት ለይተው የሚያክሙበት ኖራ መግዛታቸውንም ጠቁመዋል።

የሚፈልጉትን መጠን በሙሉ ባይኾንም ከፍላጎታቸው ከግማሽ በላይ የሚኾን የአፈር ማዳበሪያ መግዛታቸውንም ተናግረዋል። ሌላው በምሥራቅ ጎጃም አሥተዳደር የይትኖራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዳምጣቸው ቢምረው እንዳሉት ያላቸውን ሁለት ሄክታር መሬት በሙሉ በጤፍ ለመሸፈን ሁለት ጊዜ ማረሳቸውን አውስተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርም መግዛታቸውን ተናግረዋል። የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋሁን ዋስይሁንም ጤፍ፣ ገብስ እና በቆሎ የሚያመርቱበትን መሬት ደጋግመው ማረሳቸውን ጠቁመዋል። የአፈር ማዳበሪያ ዋጋው ከአምናው ጋር ሲያነጻጽሩት ጭማሪ ቢኖረውም ገዝተው አስቀምጠዋል። የበቆሎ ምርጥ ዘርም መግዛታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) ለ2017/18 የመኽር ምርት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ እና 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በማቅረብ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

የምርት ጭማሪው እንዲመጣ የሚፈለገው የሚታረስ መሬት በመጨመር አይደለም ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ ይልቁንም ማሣን ደጋግሞ በማረስ፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን በመከተል፣ ሰብልን በኩታ ገጠም በመሸፈን፣ ግብዓትን በተሻለ ኹኔታ በመጠቀም እንደኾነም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር የሚኾነው የእርሻ መሬት በአሲዳማ አፈር የተጠቃ ነው ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ ለዚህ ማከሚያ ደግሞ ኖራ ተገዝቶ እየተሰራጨ ይገኛል።

በአማራ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 170 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ዶክተር ማንደፍሮ አስታውሰዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ሕግ አንድነት እና ልዩነት፦
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሮች ሹመት ሰጡ።