በባሕር ዳር ሁለት አካባቢዎች በመኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ፤ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

227

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በሁለት አካባቢዎች የእሳት አደጋ ደርሷል፡፡ አደጋው የደረሰው ቀበሌ 8 በሚገኝ የመኖሪያ ቤት እና ቀበሌ 12 አካባቢ በሚገኙ የሞባይል መሸጫ የገበያ ማዕከላት ላይ ነው፡፡
ቀበሌ 8 ከሌሊቱ 5፡50 አካባቢ ከአንድ መኖሪያ ቤት የተነሳ እሳት መኖሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲወድምና ከጎረቤት ያለ ሌላ ቤት ላይ መጠነኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡ የእሳት አደጋው በመኖሪያ ቤቶቹና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በቀር በሰው ሕይወትም ሆነ በአካል ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ቀበሌ 12 ማለትም ከነባሩ የአውቶቡስ መናኸሪያ ጀርባ (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጣና ቅርንጫፍ ጎን) ከሚገኘው ሰላም የሞባይል የገበያ ማዕከል ላይም የእሳት ቃጠሎ ደርሷል፤ በአደጋውም 48 ሱቆች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ሁለት የገበያ ማዕከላት ባሉት የሞባይል የገበያ ማዕከል የተነሳው እሳት ሁሉንም ሱቆችና በውስጣቸው የነበረውን ንብረት ማውደሙን የሱቆቹ አከራይ ሀጂ ተዘራ አበበ ተናግረዋል፡፡

ከገበያ ማዕከላቱ የአንደኛው የጥበቃ ሠራተኛ ወጣት የሺዋስ መላኩ ሌሊት 9፡30 አካባቢ ላይ የእሳትቃ ቃጠሎ ጪስ ሲሸትተው አሰሳ እንዳደረገና ከኋላ በኩል መካከል ላይ ከሚገኝ ሱቅ ጭስ ማየቱን ከዚያም ፍንዳታ መከሰቱን ለአብመድ ተናግሯል፡፡ ወዲያውኑ ለተለያዩ ባለሱቆች ስልክ ቢደውልም ብዙዎች እንዳላነሱለትና የሱቆቹ አከራይ ሀጅ ተዘራ ግን ስልክ አንስተውለት እንዳሳወቀ አቶ የሺዋስ ተናግሯል፡፡ አቶ የሺዋስ የአደጋው መንስኤ የሞባይል ባትሪ መፈንዳት ሳይሆን እንደማይቀር ግምቱን ተናግሯል፡፡

አቶ የሺዋስ ባደረገው የድረሱልኝ ጥሪም ወጣቶች፣ የፀጥታ ኃይል አባላት፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ መኪና ደርሰው ወደ ሌሎች ሱቆችና ድርጅቶች ሳይስፋፋ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል፤ ፖሊስም የወጣቶችን፣ የፀጥታ ኃይል አባላትንና እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያና መከላከያን አመስግኗል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ታደሰ ዳኛቸው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የሱቆቹ ባለቤቶች በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ ለመስጠት ወደ ፖሊስ ጣብያ በመሄዳቸው አብመድ ለጊዜው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻለም፡፡

ፖሊስ ዝርዝር የአደጋውን ጉዳይ መርምሮ የደረሰውን የጉዳት መጠን ይፋ እንደሚያደርግ አመላክቷል፤ በአደጋዎቹ በሰው አካልም ሆነ በሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ፖሊስም አረጋግጧል፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ

Previous articleሱዳን በ24 ሰዓታት ብቻ 325 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገለጸች፡፡
Next articleአብሮ ያላመሸ ባለጠጋነትን የማግኘት ተስፋ …፡፡