
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕጎች በፍትሐ ብሔር እና በወንጀል ሕግ ሲከፈሉ በተሳታፊ አካላት ላይ የሚያስከትሉትን የኀላፊነት አይነት እና መሠረታዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። የሕግ የበላይነት ሲሰፍን የአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮች መልካም ይኾናሉ። ሕግ በሌለበት እና ባልተከበረበት ኹኔታ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል፤ የሀገር ሰላም ይናወጣል።
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የወንጀል አቃቢ ሕግ ዳግማዊ አገኘሁ የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ሕጉን አንድነት እና ልዩነት በተመለከተ ሲያብራሩ መንግሥት የኅብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ ሲል ሕግ በሚፈቅደው መሠረት በተግባር ላይ እንዲውሉ ያደርጋል ብለዋል።
እነዚህ ሕጎችም የፍትሐ ብሔር ሕጉን እና የወንጀል ሕጉን መሠረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል። በእነዚህ ድንጋጌዎች በመመራት የግለሰቦችን ነጻነት፣ የሕዝቦችን ሰላም እና የሀገር አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ይደረጋል ነው ያሉት። አሁን እየተገለገልንበት ያለው የፍትሐ ብሔር ሕግ በ1952 ዓ.ም የወጣ እንደኾነ ተናግረዋል። የፍትሐ ብሔር ሕጉ የተጎዳ ሰው፣ የተዘረፈ ሰው፣ መካስ ያለበት ሰው በአጠቃላይ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አማካኝነት መብት እና ጥቅሙ እንዲከበርለት በግልጽ ያስቀመጠ ነው ይላሉ አቃቢ ሕጉ ዳግማዊ አገኘሁ።
የፍትሐ ብሔር ዓላማ በንብረት፣ በአካል፣ በፍላጎት እና ጥቅም ላይ የተፈጸሙ ጉዳቶችን በካሳ መልክ ወደነበሩበት መመለስ ነው ብለዋል። የወንጀል ሕጉን በተመለከተ ደግሞ በ1952 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የወጣ ነው። በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ለብዙ ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ እንደነበርም አንስተዋል።
ነገር ግን በ1952 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ማለትም የኢኮኖሚ ማደግ፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች መጎልበት ወዘተ በልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ተሻሽሏል ብለዋል። ይህም በአዋጅ ቁጥር 214/1974 ዓ.ም ወጥቶ በሥራ ላይ እንደቆየ አቃቢ ሕጉ አብራርተዋል።
አኹን በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ደግሞ እነዚህን በማሻሻል የወጣ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህም የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/1996 ዓ.ም ተብሎ ተደንግጎ አኹን በተግባር ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ይህ የወንጀል ሕግ ሥራ ላይ የዋለው ከግንቦት 01/1997 ዓ.ም ጀምሮ እንደኾነም ገልጸዋል። የወንጀል ሕግ ድንጋጌ በማስረጃ እርግጠኝነት ሲታይ አንድ ሰው ማድረግ የሌለበትን ተግባር ሲያደርግ እና አድርግ የተባለውን ደግሞ ባለማድረጉ ምክንያት ተጠያቂ የሚኾንበትን መንገድ የሚመለከት ጉዳይ እንደኾነ ተናግረዋል።
ግለሰቡን አስመልክተው የሚቀርቡ ክሶች ከጥርጣሬ በላይ ኾነው የተገኙ ናቸው ነው ያሉት። በማስረጃዎችም የተረጋገጡ መኾን አለባቸው ብለዋል አቃቢ ሕጉ። በወንጀል ሕጉ ላይ አጠራጣሪ ማስረጃዎች በቂ አይኾኑም ነው ያሉት። በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ግን አሸናፊ የሚኾነው የተሻለ ማስረጃ ይዞ የቀረበው አካል ይኾናል ብለዋል።
ስለዚህ በፍትሐ ብሔር ሕጉ እና በወንጀል ሕጉ የሚታዩ ጉዳዮች ከሚቀርቡ ማስረጃዎች አንጻር እና ከሚመለከቱበት መነጸር አንጻር ልዩነት አላቸው ማለት ነው። ስለዚህ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ተከሳሽም ኾነ ከሳሽ ላይ አሸናፊነቱ የሚረጋገጠው በሚቀርብ መረጃ እና ማስረጃን መሠረት በማድረግ ሲኾን በወንጀል ሕጉ ግን ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ ኾኖ የተገኘን እና እርግጠኛ የኾነን ጉዳይ ይመለከታል ነው ያሉት።
ሌላው ልዩነታቸው ብለው ያነሱት ደግሞ በወንጀል ሕጉ ላይ ይህን አድርግ፣ ይህን አታድርግ ተብሎ በእያንዳንዱ ነገር መተርጎም፣ መቅረብ ወይም በሕጉ ድንጋጌ ላይ መቀመጥ አለበት ይህም ሲባል በአናሎጅ በማመሳሰል አይተረጎምም ይላሉ። በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ግን ይላሉ አቶ ዳግማዊ አገኘሁ የፍትሐ ብሔር ድንጋጌውን አመልካች በኾነ መንገድ በማመሳሰል ሊተረጎም ይችላል ነው ያሉት።
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በማመሳሰል ወይም በአናሎጅ ወንጀልን መተርጎም አይቻልም ተብሎ ተቀምጧል። እያንዳንዱ ወንጀል በደንብ ተዘርዝሮ መቀመጥ አለበት እንጅ ብለዋል። በሕግ እና በደንብ ካልተደነገገ በቀር ወንጀል የለም፤ ሕግ በግልጽ ካላስቀመጠው በስተቀር ቅጣት የለም ነው ያሉት። በወንጀል ሕጉ ከተቀመጡ ቅጣቶች ውጭ ሌላ ቅጣት ሊቀጣ አይችልም ብለዋል።
በፍትሐ ብሔር ሕጉ ግን በማመሳሰል መወሰን እንደሚቻልም ተቀምጧል ነው ያሉት። ሌላው ልዩነት ብለው ያነሱት ነጥብ ደግሞ በወንጀል ሕግ ባለቤትነት ነው። በወንጀል ሕጉ መሠረት ከሳሽ የሚኾነው መንግሥት ነው። መንግሥትን ወክሎ አቃቢ ሕግ ክስ ያቀርባል። የፍትሕ ተቋም እስከታች ድረስ ሰንሰለቱን ዘርግቶ እና አቃቢ ሕጎችን አዘጋጅቶ ክሶችን ይከታተላል ብለዋል።
ለምሳሌ የግድያ ወንጀሎች፣ የስርቆት ወንጀሎች፣ የዘረፋ ወንጀሎች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ወዘተ ከባድ ወንጀሎች በመንግሥት ኀላፊነት ወይም አቃቢ ሕግ ክስ መስርቶ የሚከላከልባቸው ጉዳዮች ናቸው። ነገር ግን በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ምሳሌ ስድብ፣ ዛቻ፣ ማዋረድ፣ ስም ማጥፋት ወዘተ አቤቱታ ከቀረበ ይጣራል አቃቢ ሕግ ክሱን ያቀርባልም ይላሉ። በፍትሐ ብሔር ሕጉ ግን አቤቱታውን የሚያቀርቡት ራሳቸው ባለቤቶቹ ናቸው ይላሉ።
ሌላው ልዩነታቸው ደግሞ የሃሳብ ከፍል ነው። ይህም ሲባል አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው መኾን እንዳለበት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ተደንግጓል ብለዋል። በፍትሐ ብሔር ሕግ ግን ይላሉ አቃቢ ሕጉ ከሳሽ እና ተከሳሽ ግለሰቦች በፍትሐ ብሔር ኀላፊነት ከዚህ የተለየ ሞራላዊ ሃሳብ ማለትም የቸልተኝነት ሃሳብ ባልተሟላበት ኹኔታ ሊከሰሱ እንደሚቸሉ ተቀምጧል ብለዋል።
በወንጀል ጉዳይ የተከሳሽ ዝምታ የሚባል ጉዳይ አለ። የሚከሰስ ሰው ዝም ካለ ወይም ተከሶ ቀርቦ መልስ አልሰጥም ካለ ወንጀል አልፈጸምኩም እንዳለ ተደርጎ በመዝገብ ላይ ይጻፋል። በፍትሐ ብሔር ሕጉ ግን ተከሳሽ የተከሰሰበትን ጉዳይ በዝርዝር ካላስቀመጠ በስተቀር እንዳመነ ተቆጥሮ ፍርድ ይሰጥበታል ነው ያሉት።
ይህ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 23/2 እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 133/1 ላይ የተቀመጠ ጉዳይ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ስለዚህ ዝምታ በወንጀል ሕጉ ጥፋት እንዳላጠፍ ይቆጥራል፤ ዝምታ ወይም የተከሳሽ መልስ አለመስጠት በፍትሐ ብሔር ሕጉ ደግሞ ጥፋቱን አምኗል የሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል ማለት ነው፤ ጥፋተኛ ተደርጎም ይፈረድበታል ብለዋል።
በሌላ መንገድ በወንጀል ሕጉ ላይ ተከሳሽ ከሞተ ክሱ ይቋረጣል። በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ግን የተከሳሽ መሞት ክሱን ሊያቋርጠው አይችልም ይላሉ አቃቢ ሕጉ። ጥቅም ያለው ግለሰብ ክሱ እንዲቀጥል እና ካሳውን እንዲያገኝ ማድረግ ይችላል ብለዋል። የሚወሰዱ ርምጃዎችንም በተመለከተ በወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ በእስራት ይቀጣል፤ በገንዘብም ይቀጣል። በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ግን ገንዘብ ብቻ እንደሚቀጣም ያላቸውን ልዩነት አብራርተዋል።
በወንጀል ጉዳይ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ወይም ከ15 እስከ 18 ዓመት የኾኑ አጥፊዎች በወንጀል ሕጉ ይጠየቃሉ። በፍትሐ ብሔር ሕጉ መሠረት ግን ሊጠየቅ እንደማይችል ተቀምጧል ነው ያሉት። የሚጠየቁባቸው ግን ልዩ መንገዶች እንዳሉ ጠቁመዋል። የሁለቱ ሕጎች አንድነትን በተመለከተ ሁለቱም መንግሥት ያወጣቸው ሕግጋት ናቸው። ይህም ለኅብረተሰቡ ጥበቃ እና ደኅንነት ተብለው የወጡም መኾናቸው ያመሳስላቸዋል ነው ያሉት።
የሁለቱንም ሕጎች አፈጻጸም መንግሥት ይከታተላቸዋልም ብለዋል።
በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
