
ከሚሴ:ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በጤናው ዘርፍ ያለው አገልግሎት ምቹ እና ቀልጣፋ እንዲኾን የሚያግዙ አምቡላንሶች እና ሞተር ሳይክሎችን ለኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስተላልፏል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩም ከጤና ቢሮው የተረከባቸውን እና ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸውን አምቡላንሶች እና ሞተር ሳይክሎችን ለወረዳዎች አድርሷል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የተገኘውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አምቡላንሶችን ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለወረዳዎች የተላለፉት አምቡላንሶች በአምቡላንስ እጥረት ሳቢያ በነፍሰጡር እናቶች እና በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ኡስማን አሊ የክልሉ ጤና ቢሮ ዘጠኝ ሞተር ሳይክሎችን እና አምስት አምቡላንሶችን ከ 33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ አስረክቧል ነው ያሉት።
አምቡላንሶቹ በገጠር ወረዳዎች በአምቡላንስ እጥረት ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን እና ሞትን ለመቀነስ የሚሠራውን ሥራ የሚያግዙ መኾናቸውን አስረድተዋል።
አምቡላንሶቹ የተላለፉላቸው የወረዳ የጤና ጸሕፈት ቤት ኀላፊዎች ከዚህ በፊት በአምቡላንስ እጥረት የሚሞቱ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል። አሁን ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
