ሕዝብ መከላከል በሚችላቸው በሽታዎች እንዳይጠቃ ጠንካራ የተግባቦት ሥራ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

25

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ፎረም እያካሄደ ነው። በፎረሙ ላይ የመገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች ተሳትፈዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል። በተለይም ድንገተኛ እና ተላላፊ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና በቁጥጥር ስር ለማዋል ጠንካራ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ነገር ግን ትኩረት ያላገኙ እንደ ትራኮማ፣ ወስፉት እና ኮሶ አይነት በሽታዎች በሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ማኅበረሰቡን ማስገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሕዝባችን መከላከል በሚችላቸው በሽታዎች መጠቃት የለበትም ያሉት ምክትል ኀላፊው የመገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራውን በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የወባ በሽታ መከላከል የምንችለው በሽታ ነበር፤ ነገር ግን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በወረርሽኝ መልኩ ተከስቶ አምራች ኀይል ታሞ እንዲተኛ አድርጓል ነው ያሉት። ይህንን በውል መገንዘብ እና በሽታን ቀድሞ የመቆጣጠር ማኅበረሰባዊ ንቃት ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የክልሉን ሕዝብ ጤና እና የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በርካታ የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የቢሮውን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ለሚዲያ መሪዎች እና ባለሙያዎች ያቀረቡት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ክትትል እና ምዘና ዳይሬክተር አማረ ሹመት የጤና ፈጠራን በማበልጸግ አዳዲስ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን የማሻሻል ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ዘመናዊ የጤና ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችሉ የጤና ተቋማት ግንባታዎች እየተካሄዱ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ 289 አዲስ እና ነባር የጤና ተቋማት ግንባታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም 38ቱ በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ ተጠናቅቀዋል። ቢሮው ዘመናዊ እና ዲጂታል አሠራሮችን እየዘረጋ መኾኑንም ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በ10 ጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል። በ160 ጤና ጣቢያዎች ለነፍሰጡር እናቶች የአልትራ ሳውንድ ሕክምና በማመቻቸት ሪፈርን የሚቀንስ አገልግሎት መስጠት ተችሏልም ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ የክልሉ ጤና ቢሮ የ10 ቢሊዮን 333 ሚሊዮን 404 ሺህ ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች፣ የሕክምና ቁሳቁሶች እና ኬሚካሎች ስርጭት ማከናወኑንም ገልጸዋል።

85 በመቶ የሚኾኑ ታካሚዎች የታዘዘላቸውን ሁሉንም መድኃኒቶች በታዩባቸው ሆስፒታሎች እንዲያገኙ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የዘጠኝ ወራት ክንውኑ እንደሚያሳየውም 79 በመቶዎቹ ናቸው በታከሙበት የሕክምና ተቋም ውስጥ መድኃኒት ያገኙት።

የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ከመቀነስ አኳያም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። እናቶች በጤና ተቋማት ከወለዱ 99 በመቶ የሚኾነውን የእናቶች የሞት አደጋ መቀነስ ይቻላል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 359 ሺህ እናቶች በጤና ተቋማት እና በሠለጠኑ ሙያተኞች እንዲወልዱ መደረጉንም ገልጸዋል።

በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል እና አክሞም ለማዳን የሕዝቡን የጤና ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ለዚህም በተለይም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጠንካራ የኾነ የተግባቦት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ እና አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችል ሙያዊ አበርክቷቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሀገራዊ የብልፅግና ግባችንን እና ዓመታዊ እቅዶቻችንን ለማሳካት ተቋማት ቀን ከሌት ሊተጉ ይገባል” ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።