2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች በአዲስ ፈቃድ መሰጠቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ገለጸ።

16

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የልማት ቀጣናዎች ተብለው ከተለዩት አካባቢዎች ውስጥ የምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። አካባቢው በተለይም ሰፊ ሊታረስ የሚችል መሬት እና ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ያሉበት አካባቢ ነው።

ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ያለበት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ሰብሎች የሚመረቱበት ቀጣና ነው። በዞኑ ከዚህ በፊት በአገልግሎት፣ በግብርና እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ለመሠማራት ያመለከቱ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ሲኾን በአዲስ ላመለከቱት ደግሞ ፈቃድ ተሰጥቷል።

ወደ ሥራ ከገቡት ውስጥ ደግሞ በገንዳውኃ ከተማ የሚገኘው ወንድሜነህ ፍስሃ ነዳጅ ማደያ አንዱ ነው። የድርጅቱ ሥራ አሥኪያጅ ዮሐንስ ወርቁ አካባቢው ካለው ሰፋፊ የእርሻ ልማት እና ከሱዳን ጋር በሚደረገው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት ያለበት በመኾኑ በነዳጅ ማቅረብ ሥራ እንዲሠማሩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። ከታኅሣሥ 2017 ዓ.ም ደምሮ ነጃጅ እና የሞተር ዘይት በአካባቢው ለሚገኙ ተሽከርካሪዎች እያቀረቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ለ12 ሠራተኞች በቋሚነት፣ ለ20 ሠራተኞች ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በቀጣይ ዘርፉ ወደ ካምፓኒ ሲያድግ ከ150 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በዞኑ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች ሥራውን ከማስፋት ባለፈ በምግብ ዘይት ማምረት ሥራ ለመሠማራት ጥናት እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸውልናል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ መሰንበት መልካሙ ከስድስቱ የልማት ቀጣናዎች ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው ብለዋል። አካባቢው በተለይም በግብርና፣ በእንስሳት ሃብት ልማት፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና በአምራች ዘርፎች አቅም ያለው ቀጣና መኾኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች ለመሠማራት ያመለከቱ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፤ በአዲስ ላመለከቱ ባለሃብቶች ደግሞ ፈቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት። ባለፉት ዓመታት በነዳጅ ማደያ ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ስምንት ፕሮጀክቶች ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ እና ግንባታ አጠናቅቀው አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙ እንዳሉ ገልጸዋል።

በገንዳውኃ ከተማ አሥተዳደር በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር በአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ ሦስት ባለሃብቶች መሬት የማስተላለፍ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በአገልግሎት፣ በግብርና እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለመሠማራት ፈቃድ ለተሰጣቸው ፕሮጀክቶችም መሬት ለማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።

በዚህ ዓመትም 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ለ36 ፕሮጀክቶች በአዲስ ፈቃድ ተሠጥቷል ነው ያሉት። ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ 12 ሺህ 417 ለሚኾኑ ዜጎች በቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው ተብሏል። ፕሮጀክቶች በውላቸው መሠረት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ለአካባቢው ኅብረተሰብ የቴክኖሎጅ ሽግግር በማምጣት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።

ዞኑ ከፍተኛ የኾነ ጥሬ እቃ የሚመረትበት አካባቢ በመኾኑ ባለሃብቶች በግብርና፣ በአምራች እና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሠማሩ ጥሪ አቅርበዋል። ለዚህ ደግሞ በገንዳውኃ ከተማ 40 ሄክታር የሚጠጋ መሬት መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሸለመ።
Next article“ሀገራዊ የብልፅግና ግባችንን እና ዓመታዊ እቅዶቻችንን ለማሳካት ተቋማት ቀን ከሌት ሊተጉ ይገባል” ተመስገን ጥሩነህ