
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የታጠቁ ኃይሎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግር ምክንያት በተቋማት ላይ ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት እና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገንዘብ መምሪያ አስታውቋል።
የዞኑ ገንዘብ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ማንዴ ዘሜ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ባሉ የገንዘብ ተቋማት ላይ በጸጥታ ችግሩ የደረሰባቸውን ውድመት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ታጣቂዎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች እና ሦስት ከተማ አሥተዳደሮች የገንዘብ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የኾነ የሀብት እና ንብረት ውድመት ደርሷል ብለዋል። የደረሰው ውድመትም በገንዘብ ሲገመት 44 ሚሊዮን 278 ሺህ ብር እንደኾነ ገልጸዋል።
ከዚሁ በተጨማሪም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዞኑ እየሠሩ በነበሩ ሁለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጂቶች ላይ የሰብዓዊ ሀብት እና የንብረት ውድመት ደርሷል ነው ያሉት። በዚህም አንድ የፕሮጀክት ሠራተኛ ሕይዎቱን ያጣ ሲኾን ሌሎች ሰባት ሠራተኞችን የማገት እና የንብረት ዝርፍያ ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል።
ሌሎች በዞኑ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጂቶች ሥራቸውን በሚፈለገው ልክ ማከናወን እንዳልቻሉ እና በተለይም በገጠር አካባቢዎች ኅብረተሰቡን በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፕሮጀክቶች ሥራቸውን በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳልቻሉ ነው የገለጹት።
ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮችም የውስጥ ገቢን በሚፈለገው ልክ እና በወቅቱ መሰብሰብ ባለመቻላቸው በበጀት ዓመቱ ከውስጥ ገቢ ለካፒታል በጀት ከተመደበው 143 ሚሊዮን 765 ሺህ 767 ብር ውስጥ በእስካሁኑ ሥራ ላይ የዋለው ሰባት በመቶው ብቻ እንደኾነ ገልጸዋል።
የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተቋቁመን የተቋማትን ሥራ ለማሳለጥ እና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ለዞኑ ከተመደበው ስድስት ቢሊዩን 928 ሚሊዮን 393 ሺህ 766 ብር ውስጥ እስከ የካቲት መጨረሻ 66 በመቶ የሚኾነውን ሥራ ላይ ማዋል ተችሏል ነው ያሉት።
በዞኑ የሚሠሩ 20 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በሥራቸው በሚገኙ 25 ፕሮጀክቶች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ይዘው ወደ ተግባር በመግባት ከ3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በውኃ እና ኢነርጂ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና ተፈጥሮ ሀብት፣ በሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሰላም ግምባታ ዙርያ በሁሉም ወረዳዎች በመግባት የኅብረተሰቡን ችግር እያቃለሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በመጨረሻም አገልግሎት አሰጣጥን ከመምሪያ እስከ ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል እና ለሚነሱ ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አገልግሎታችን ፈልገው የሚመጡ ደንበኞችን አርክተን ለመመለስ እየሠራን እንገኛለን ማለታቸውን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን