ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ)በሱዳን በአንድ ቀን ብቻ 325 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ ደቡብ አፍሪካም ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግባለች፡፡
በሱዳን እስከ ትናንት ግንቦት 8/2012 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 289 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገልጧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 222 ሰዎች ሲያገግሙ 97 ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
እንደ ሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ቫይረሱ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በተለይም ከጠቅላላ ታማሚዎች 1 ሺህ 874 የተገኙበት የካርቱም ክፍለ ግዛት ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ነው ሚኒስቴሩ ያሳወቀው፡፡ በዚህ የተነሳ ባለፈው ሚያዝያ ላይ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀጠል፣ ከዋና ከተማዋ ካርቱም ወደ ሌሎች ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንም መገደብ እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና በደቡብ አፍሪካም በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ታውቋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኮኖናቫይረስ የተከሰተው ባሳለፍነው መጋቢት መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ትናንት ባሉት ቀናት በሀገሪቱ 14 ሺህ 355 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል፤ 6 ሺህ 478 አገግመዋል፤ 261 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ትናንት ቅዳሜ ግንቦት 8/2012 ዓ.ም ብቻ 831 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህም በደቡብ አፍሪካ ቫይረሱ መግባቱ ከተረጋገጠ ጀምሮ ባሉት ቀናት ከፍተኛው አሀዝ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያሳወቀው፡፡
እንደ ሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ በደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ለ10 ሚሊዮን 737 ሺህ 341 ሰዎች ምርመራ ተደርጓል፡፡ በመላ ሀገሪቱም 30 ሺህ 823 የኮሮናቫይረስ ሕሙማን መንከባከቢያ አልጋዎች ያሏቸው 376 የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በማሰብ የንግድ ተቋማት እንዴት መከፈት እንዳለባቸውና የእንቅስቃሴ ገደቡንም ማላላት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ወረርሽኙን ለመከላከል ከተቋቋመው ጥምረት ጋር ትናንት ቅዳሜ መምከራቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ደግሞ ሌላ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲዜን
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡