የሆሳዕና በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሥ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

43

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሥ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከሚጾሙ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ ነው፡፡ በመሃሉ እና በማጠናቀቂያው ሳምንትም ትርጉም ያላቸው በዓላት እና ክዋኔዎች አሉት፡፡

ከነዚህ በዓላት ውስጥ አንዱ ሆሳዕና ነው፡፡ ሆሳዕና ዐቢይ ጾም ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ሲቀረው ይከበራል፡፡

የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር ቃለጽድቅ አየነው ስለ ሆሳዕና በዓል ታሪክ፣ ትውፊት፣ ይዘት እና አንደምታ አብራርተውልናል፡፡

በእብራይስጥ ቋንቋ ሆሳዕና ማለት አቤቱ አሁን አድን ማለት ነው ያሉት መምህሩ በግዕዝ ደግሞ መድኃኒት ማለት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በእግዚአብሔር ስም የሚመጣው የተባረከ ነው የተባለለት፣ ለሁሉም መድኃኒት የኾነው፣ ሆሳዕና ብለን የምንጠራው፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ወደሚል ሃሳብ ይጠቀለላል ብለዋል፡፡

ነብያት በትንቢት ሲነግሩለት እንደቆዩ እና “ሰማዩን ቀድደህ ውረድ፤ አድነን” እያሉ ሲለምኑት የነበረውም በሆሳዕና መተግበሩንም ገልጸዋል፡፡

ክርስቶስ በሆሳዕና ዕለት ወደ እየሩሳሌም ሲገባ መስቀለኛ ከኾነው ቤተ ፋጌ ላይ ቆሞ ወደ ፊታችሁ ወዳለች መንደር ሂዱና ከውርንጭላዋ ጋር ታስራ የምታገኟትን አህያ ፈትታችሁ አምጡልኝ ብሎ መናገሩን ጠቅሰዋል፡፡

መስቀለኛ መንገድ ላይ መቆሙ ሊሰቀል መኾኑን ማመላከቱ፤ የታሰሩትን ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱም የታሰሩትን ለመፍታት እንደሚሰቀል ማመላከቱ እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡

ዲያቢሎስ በበለስ ምክንያት እየሰረቀ ያሰራቸው ሌላ ጌታ ፈልገው እንደነበር፣ ደቀ መዛሙርቶቹ አህዮቹን ፈትተው እንዲያመጡለት ሲልክም፣ ቢጠየቁ ተሰርቀው መታሰራቸውን እና ፈጣሪያቸው ይፈልጋቸዋል እንዲሉ መናገሩን ተናግረዋል፡፡

በዚያውም ድርሻ ሥርዓት እያስተማረ መሆኑን መምህር ቃለጽድቅ ገልጸዋል፡፡ የክርስቶስ፣ የሐዋርያት እና የምዕመን ድርሻ መኖሩንም ጠቅሰዋል መምህሩ። የታሰሩትን እንዲፈቱ የታዘዙት ሃዋርያት በምድር ላይ የፈታችሁት በሰማይም የተፈታ ነው መባሉን እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል፡፡ ታስረው የነበሩት ሲፈቱ የክርስቶስ ማደሪያ እንደኾኑም ማሳየት ነው ብለዋል፡፡

ክርስቶስ በተናቀችዋ አህያ ላይ ሆኖ የሄደው አህያ ለልጇ መስዋዕትነት በመክፈል ጠንካራ መሆኗን ጠቅሰው ክርስቶስም ፍቅር ባላቸው ሰዎች መካከል አድራለሁ ማለቱን ለመተግበር መኾኑን አመላክተዋል፡፡

አህያ አላፊ አግዳሚ የሚጭናት እና ትሁት እንደኾነች፣ ፍቅር እና ትህትና ያላት አህያ ምዕመናንን ስለምትወክል ኢየሱስም ትሁቶችን፣ የወደቁትን እና የተዋረዱትን ከፍ ለማድረግ ወደ ምድር እንደመጣ ለማጠየቅም ነው ብለዋል፡፡

በትንቢተ ዘካርያስ ምዕራፍ 9 የእስራኤል ልጅ እነሆ ንጉስሽ በአህያ ተጭኖ ይመጣል፤ ጻድቅ እና የዋህ ሆኖ ይመጣል በሏት የተባለውን መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡

ነብያት መጪው ዘመን የጦርነት፣ የቸነፈር እና የረሃብ ከሆነ በፈረስ እና በቅሎ ሆነው፣ ጥቁር ለብሰው፣ ጦር ይዘው ይመጣሉ፡፡ መጪው ዘመን ሰላም ከኾነ ደግሞ ነጭ ለብሰው፣ መነሳንስ ይዘው እና በአህያ ጀርባ ላይ ሆነው እንደሚመጡ ጠቅሰው ክርስቶስም መጪውን ጊዜ በመስቀሉ ሰላም ሊያደርግ ስለሆነ በአህያዋ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡

እሳተ መለኮት ክርስቶስን ለተሸከመችው አህያ ክብር እና እንክብካቤ እንደተደረገ ሁሉ በዛሬው ዘመንም ወጣቶች ክርስቶስ ያደረበትን የቃል ኪዳኑን ታቦት ለተሸከሙት ካህናት ደፋ ቀና ብለው ክብር ይሰጣሉ ብለዋል፡፡

መስቀሉን ቤተ ክርስቲያን አክብራ የያዘችው ከአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እና ከድንግል ማርያም ቀጥሎ የሚጠራ እና ክብሩ ከፍ ያለውም ክርስቶስ ስለተሰቀለበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ክርስቶስ ያረፈበት ሁሉ ክብር ይገባዋል፤ ትልቅ ነውና፤ ስለሆነ በደሙ ቀድሶታልና ያሉት መምህር ቃለጽድቅ ይህንን ሁሉ ለማሳየት መምጣቱንምገልጸዋል።

እግዚአብሔር አብርሐምን ከአንድ መቶ ዓመት እድሜው በኋላ ትወልዳለህ ሲለው አብርሐምም እየሰገደ ስቆ የነበረ ቢሆንም ልጅ ሲያገኝ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ አምላኩን ማመስገኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይስሐቅም ያዕቆብን ሲወልድ እንዲሁም እስራኤላውያንም ኤርትራን ሲሻገሩ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ማመስገናቸውን አብራርተዋል፡፡

ቤተክርስቲያንም የትውፊት ሰንሰለትን ጠብቃ የወረሰችውን እንዳይዘነጋ የቆየውን የማመስገን ሥርዓት ማስቀጠሏን ገልጸዋል፡፡ ዛሬም አሁን አድን የሚለውን የእስራኤልን ሆሳዕና ንግግር በግዕዝ መድኃኒት ብላ በመተካት እያስቀጠለች ነው ብለዋል፡፡

በሆሳዕና ዕለት ምዕመናን ከዘንባባው ቅጠል መስቀል ቅርጽ እየሠሩ በራሳቸው እና በጣታቸው ላይ የሚያስሩትም በሆሳዕና ዕለት የተፈጸመውን ለማስታወስ እና በዓሉን በስዕል እና በቅርጽ ለመግለጽ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ፍቅር ሲል የማይሞተው ሞቶ፣ በትንፋሹ መጥፋት በሚችሉ ጠላቶች ተይዞ፣ ተደብድቦ፣ ተገርፎ፣ መስቀል ተሸክሞ፣ ሁሉን በትዕግሥት ችሎ በመጨረሻ ግን ያሸነፈ መኾኑን ቤተ ክረስቲያን እንደምታስተምር አብራርተዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በመዓት ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው እንዳለው በመሞት ማሸነፍን ክርስቶስ አሳይቶናል፡፡ በመሸነፍ ማሸነፍን ትውልዱ እንዲወስድ በተግባር አስተምሮናል ነው ያሉት፡፡ ሁሉን ነገር በፍቅር በማድረግ ማሸነፍ እነደሚቻልም ነው መምህር ቃለጽድቅ የተናገሩት፡፡

ሰዎችም በዓሉን ሲያከብሩ ተሸንፎ ማሸነፍን እና ለሰው ተላልፎ መሞትን መማር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ: ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት!
Next articleበግጭት ምክንያት ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት እና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገንዘብ መምሪያ አስታወቀ።